የአባይ ወንዝ ቅየሳ የግንቦት20 በአል ማድመቂያ ሆኖ ዋለ

ግንቦት ፳ (ሀያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መንግስት የአባይን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየስ የግንቦት20 በአልን ሲያከብር ቢውልም ሰራተኞች ግን ስራው ለበአል ተብሎ በይድረስ ይድረስ እንደሰራ በመደረጉ የታቀደው አልተሳካም ይላሉ።

መንግስት የግንቦት20 በአልን አባይን የፍሰት አቅጣጫ በማስቀየር ለማክበር ማቀዱን በዚህም የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስደመም ወይም በእንግሊዝኛው አጣራር ሰርፕራይዝ ለማድረግ ማቀዱን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።

ዛሬ ግድቡ በሚሰራበት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የመንግስት  ባለስልጣናት በተገኙበት የወንዙ አቅጠጫ መቀየሩ ተበስሯል።

በስፍራው ላይ ያነጋገርናቸው ሰራተኞች እንደገለጹት ከሆነ የውሀውን አቅጣጫ የማስቀየሩ ስራ ለግንቦት20 በአል እንዲደርስ ተብሎ በይድረስ ይድረስ የተሰራ በመሆኑ፣ መንግስት በቴሌቪዥን ቀርጾ ለማሳየት የፈለገውን ሳያሳካ ቀርቷል። ‘

ሰራተኞች እንደሚሉት በይድረስ ይድረስ የተሰራ ስራ በመሆኑ የውሀ ማስቀየሻው ግድብ ግንባታ 1 ሜትር ከ30 ሴንቲሜትር ሲቀረው እንዲቋረጥ ተደርጓል። በዚህም የተነሳ ውሀ ወደ ግድቡ በመግባቱ መንግስት ለማሳየት የፈለገውን ሳያሳይ ቀርቷል።

የውሀውን አቅጣጫ የማስቀየሩ ስራ የፕሮጀክቱ ትልቁ አካል ተደርጎ በባለስልጣናት መነገሩንም ሰራተኞች አልተቀበሉትም። ከዚህ በሁዋላ ከ85 በመቶ ያላነሰ ስራ ይጠብቀናል በማለት ሰራተኞች ለኢሳት ግልጸዋል።

የአባይ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 2 አመታት ሲሆነው፣ መንግስት  እስከ 20 በመቶ የሚደርስ ስራ መሰራቱን ይናገራል። 80 በመቶ የሚሆነው ቀሪው ስራ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ይጠናቀቃል የሚለውን ሰራተኞች አይቀበሉትም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግንቦት20ን በመደገፍ ለድጋፍ ሰልፍ ያልወጡ የወሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወደ ግቢ እንዳይገቡ ታግደው መዋላቸውን ተማሪዎች ገልጸዋል።

የዩኒቨርስቲው ዲን አስተላለፉት በተባለው መመሪያ፣ ሰልፍ ለመውጣት ፈቃደኛ ያልሆኑ ተማሪዎች ሰልፈኞቹ ድጋፋቸውን አሳይተው ወደ ግቢያቸው እስከሚመለሱ ድረስ ወደ ግቢ እንዳይገቡ በዘበኞች ተከልክለው ውለዋል

በጉዳዩ ዙሪያ የዩኒቨርስቲውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።