አለማቀፍ መንግስታት እና ድርጅቶች በእነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ አወገዙ

ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለእየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በአል በሰላም አደረሳችሁ

ሚያዚያ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በወጣቱ ፖለቲከኛ አንዱአለም አራጌ፣ በእውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ በናትኤል መኮንን፣ ክንፈሚካኤል ደበበ ፣ ምትኩ ዳምጤ ፣ ዮሃንስ ተረፈ ፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁን አለም እንዲሁም አንዱአለም አያሌው ላይ የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ   ሚያዚያ 24፣ 2005 ዓም   ማጽደቁ አለማቀፍ ውግዘት እያስከተለ ነው።

የአለማቀፉን የጸረሽብር ትግል የምትመራው እና የኢትዮጵያ መንግስት ደጋፊ ተደርጋ የምትታው አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩዋ በኩል ውሳኔውን ከማውገዝና እስረኞቹ እንዲፈቱ ከመጠየቅ አልፋ የጸረ ሽብር ህጉ እንደገና እንዲታይ ጠይቃለች። ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የጠቀሱት ቃል አቀባዩ መንግስታቸው የህሊና እስረኞቹ እንዲፈቱ አስፈላጊውን ጫና እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

” በዛሬው ውሳኔ አሜሪካ በጣም አዝናለች። ውሳኔው በኢትዮጵያ ውስጥ መንግስትን በሚተቹት ላይ ሁሉ  በፍርድ ስም የሚሰጠው የፖለቲካ ውሳኔ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የሚያጠናክር ነው። አሜሪካም ጋዜጠኞቹ እንዲፈቱ አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ታደርጋለች ብለዋል ቃል አቀባዩ ።

የተለያዩ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችም በህሊና እስረኞች ላይ የተላለፈውን ውሳኔ በማውገዝ መንግስት የአለማፍ ህግ ማክበሩን ለማሳየት የነበረውን አንድ እድል በድጋሜ አበላሸ ብለዋል። ፍሪድም ናው፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሲቪከስ፣ ወርልድ አልያንስ ፎር ሲትዝንስ ፓርቲሲፔሽን፣ ኮሚቴ ቱ ፍሪ እስክንድር ነጋ፣ ኢስት ኤንድ ሆርን ኦፍ አፍሪካ   ዘ ኤልክትሮኒክ ፍሮንቲየር ፋውንዴሽን ፣ ኢንግሊሽ ፔን ፣ ዘ ኢንተርናሽናል ፕሬስ ኢንስቲቲዩት፣ ዘ ኢንተርናሽናል ውሜንስ ፋውንዴሽን፣ ሚዲያ ሌጋል ዲፌንስ ኢንሸቲቭ፣ ዘ ናሽናል ፕሬስ ክለብ፣ ፔን አሜሪካን ሴንተር፣ ፔን ካናዳ፣ እንዲሁም ዘ ወርልድ አሶሴሽን ኦፍ ኒውስ ፔፐርስ ኤንድ ኒውስ ፐብሊሸርስ በጋራ ባወጡት መግለጫ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ የተላለፈውን የ18 አመት እስራት ከማውገዝ ባለፈ፣ መንግስት ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየንና ሌሎችንም የህሊና እስረኞች ማሰሩ መንግስት የጸረ ሽብር ህጉን በመጠቀም ጠንካራ ትችቶችን የሚያቀርቡት ለመምቻነት ማዋሉ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ያለውን ፍላጎት ጥያቄ ውስጥ የሚከት መሆኑን ገልጸዋል።

 

ውሳኔው ከተላለፈ በሁዋላም የተባበሩትን መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እስክንድር ነጋ እያንዳንዱዋን ቀን በእስር ቤት ባሳለፈ ቁጥር ፣ መንግስት የፖለቲካና ሲቪክ መብቶችን ለማክበር የገባውን ቃል ኪዳን እየጣሰ መሆኑን ሊያውቀው ይገባል ብሎአል።

 

በሌላ በኩል ደግሞ 16 አመት የተፈረደበት ክንፈሚካኤል ደበበ ወላጅ እናት የ70 አመት አዛውንቷ ወ/ሮ ብጽዓት ሀይለጊዮርጊስ ልጃቸው ንጹህ እና ምንም ወንጀል የሰራ አለመሆኑን ገልጸው ፍርድ ቤቱ የ5 አመት የእስር ጊዜ ቅናሽ ማድረጉ እንዳላስደሰተቻው ገልጸዋል

ልጃቸው እውነቱን ይዞ በመታገሉ በጣም እንደሚኮሩ የገለጹት ወ/ሮ ብጽአት ፣ ልጃቸው አሸባሪ በመባሉ ማዘናቸውንም አልሸሸጉም