የታዋቂው ጸሀፊ አስገደገ ገብረስላሴ ሁለተኛ ልጅ ታሰረ

ሚያዚያ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የህወሀትን የበረሀ ትግል ታሪክ የሚዘክረውን ገሀዲ ቊጥር አንድ፣ ሁለት እና ሶስት የሚሉ መጽሀፎችን ከመጻፍ በተጨማሪ በትግራይ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በማጋለጥ የሚታወቁት አቶ አስገደ ገብረስላሴ ሁለተኛ ልጅ ታስሯል።

የ28 አመቱ የማነ አስገደ ገብረስላሴ የሶፍት ዌር ኢንጂነረግ ምሩቅ ሲሆን፣ በውቅሮ በመምህርነት ሙያ ተቀጥሮ ነበር። አዲሱን ስራውን ሲጀምር አቶ አስገደ ልጅ መሆኑ በመታወቁ በቅጣት ወደ በረሀ ተመድቦ እንደነበር አባቱ አቶ አስገደ ገልጸዋል።

እናቱ ሻለቃ ግደይ  ወ/ሚካኤል ልጃቸውን አያቱ ወደ ሚኖሩበት አዳህላይ ወደ ምትባል ቀበሌ ለህክምና  መውሰዳቸውን ተከትሎ በቀበሌው የሚገኘው ትምህርት ቤት በመቃጠሉ የህወሀት ባለስልጣናት ህዝቡን ሰብስበው ” ትምህርት ቤቱን ያቃጠለው አቶ አስገደ የሚባል የአረና ትግራይ ድርጅት አባል  ልጅ ነው በማለት” ሊወነጅሉ ሲሞክሩ ህዝቡ ” ሀሰት ነው ” በማለት በመቃወሙ ባለስልጣናቱ ሳይሳካላቸው እንደቀረ  አቶ አስገደ ገልጸዋል።

ስብሰባው ከተበተነ በሁዋላ እና ህዝቡ ወደ ቤቱ ከገባ በሁዋላ ፖሊሶቹ ልጃቸውን አስሮ መውሰዱን ተናግረዋል።

ሌላው በእስር ላይ የሚገኘው የ26 አመቱ አክህፎም አስገደ 06 እየተባለ ከሚጠራው ድብቅ እስር ቤት ወጥቶ ወደ ሌላ እስር ቤት መዛወሩን አቶ አስገደ ገልጸው፣ አለም ባደረገው ጫና ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ ልጃቸውን በአይናቸው ለማየት እንደቻሉ እና ከወር በሀዋላም ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ አክለዋል።

 

አቶ አስገደ  በትግራይ ክልል ውስጥ በርካታ ቤርሙዳ እየተባለ የሚጠራ እስር ቤት መኖሩን አውስተዋል።

“የእነሱ ልጆች በህዝብ አንጡራ ሀብት ይማራሉ፣ የኛ ልጆች ይህን የተበላሸ ኑሮ ችለው በኖሩ በእንዲህ አይነት እስር ቤት ማሰቃየት ከዚህ በላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የለም ብለዋል::