የፌደራሉ ጠቅላይ ፍድር ቤት በአቶ አንዱዓለም አራጌ መዝገብ በተከሰሱት የህሊና እስረኞች ላይ የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ አጸና

ሚያዚያ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሀሙስ ሚያዚያ 24 ቀን 2005 የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወጣቱ ፖለቲከኛ አንዱአለም አራጌ፣  የ2012 የፔን ኢንተርናሽናል ሽልማት አሸናፊ በሆነው እውቁ ጋዜጠኛ እስክንድ ነጋ እና በሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች የቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ አድርጎ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የ18 ዓመት እስር ውሳኔ አጽንቷል።

መሀል ዳኛው አቶ ዳኜ መላኩ ለረጅም ጊዜ ቀጠሮ ሲሰጡ ከቆዩ በሁዋላ በመጨረሻም የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ ማጽደቃቸውን ገልጸዋል።

አቤቱታ ካቀረቡት መካከል የአቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ ፍርድ ብቻ ከ25 አመት ወደ 16 ዓመት ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ የወንጀል ችሎት ፥ በአቶ አንዱአለም አራጌ የእድሜ ልክ ፣ በአቶ እስክንድር ነጋ የ18 አመት ፣ በአቶ ናትናኤል መኮንን የ18 አመት ፣ በአቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ የ25 አመት ፣  በአቶ ዮሃንስ ተረፈ የ14 አመት ፣ በሻምበል የሺዋስ ይሁን አለም የ15 እና በአቶ አንዱአለም አያሌው የ14 አመት የእስራት ቅጣት ማስተላለፉ ይታወቃል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከውሳኔው በሁዋላ “እውነት ነጻ ታወጣኛለች፣ እውነት ትመነምናለች እንጅ አትብጠስም” በማለት ሲነጋር ተደምጧል። እስክንድር ደጋፊዎቹን አይዞአችሁ በማለት ሲያጽናና እንደነበር የአይን እማኞች ገልጸዋል።

ከፍርድቤቱ ሲወጡ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው አንድ የህግ ባለሙያ ፍርድ ቤቱ የሰጠው የፍርድ ሳይሆን የፖለቲካ ውሳኔ ነው ብለዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናት የ2007  የአለማቀፍ ሴቶች የሚዲያ ፋውንዴሽን አሸናፊ እና የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል መጀመሪያ ከተፈረደበት ቀን በላይ የዛሬው ፍርድ እንዳሳዘናት ገልጻለች።

የአለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት ( ሲፒጄ) የአፍሪካ ዳይሬክተር ሚ/ር ሙሀመድ ኬታ ለኢሳት እንደገለጹት ” ይህ ውሳኔ ሽብርተኝነት ከባድ ወንጀል መሆኑን ዋጋ የሚያሳጣ፣ ለፖለቲካ ፍላጎት ተብሎ  ፍትህ ሲደረመስ ያሳየ  እና የኢትዮጵያን አለማቀፍ ደረጃ ዝቅ ያደረገ መሆኑን ” ጠቅሰው የተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶችና መንግስታት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች ጋዜጠኖች እንዲፈቱ መጠየቃቸውን፣ መንግስት በያዘው ግትር አቋም የተነሳ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ እየተገለለ መምጣቱን ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፣ ርእዮት አለሙንና ውብሸት ታየን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞችን ለማስፈታት ምን አማራጭ አለ ተብለው የተጠየቁት ሚ/ር ሙሀመድ “መንግስት እስክንድርን በማሰር ጸጥ ለማሰኘት ተስፋ አድርጎ ይሆናል፣  ነገር ግን እስክንድርን በማሰሩ ጋዜጠኛውን አለማቀፍ ጀግና አድርጎታል፤ መንግስት ጋዜጠኞችን እስካልፈታ ድረስ አለማቀፍ ጫናው ይቀጥላል ” ብሎአል።