የታላቁ ሰማእት የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ተነሳ

ሚያዚያ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከአዲስአበባ የቀላል ባቡር ዝርጋታ ጋር በተያያዘ ይነሳል በመባሉ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ የነበረው የአቡነ
ጴጥሮስ ሐውልት ዛሬ ለዓመታት ከቆመበት የክብር ቦታ ተነሳ፡፡
መንግስት ሐውልቱ በድንገት ለማንሳት በሞከረበት ሰዓት የአዲስአበባ ሕዝብ ያለምንም ጥሪ በመሰባሰብ ሒደቱን
የተከታተለ ሲሆን  ሐውልቱ ከተነሳ በኋላ በእንጨት ሳጥን ውስጥ ታሽጎ በሎቤይድ ተሸከርካሪ ተጭኖ ወደ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ቅጥር ግቢ ተጓጎዞአል፡፡
በዛሬው ዕለት ረፋድ ጀምሮ ሐውልቱን ለማንሳት በተደረገው እንቅስቃሴ ወደ አ/አ ማዘጋጃ ቤትና ፒያሳ አካባቢ
ከፍተኛ የትራፊክና ህዝብ መጨናነቅ ተስተውሏል፡፡ መንግስት በሒደቱ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል በሚል ግምት ከፍተኛ
የፖሊስ ጥበቃ ሃይል በግልጽ፣ የታጠቁ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን በስውር አሰማርቶ የታየ ቢሆንም ይህ ዜና
እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ተቃውሞ አልተነሳም።
የባቡሩን ግንባታ ተከትሎ የአቡነ ጼጥሮስ ሐውልት እንደሚነሳ በታወቀበት ወቅት የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑትን
ሰማዕት ሐውልት ከማንሳት ለባቡሩ የዲዛይን ለውጥ ቢደረግለት ይሻላል ያሉ ወገኖች ተቃውሞአቸውን በአገር ውስጥና
በውጪ አገር ያሰሙ ሲሆን መንግስት በበኩሉ ሐውልቱ በጊዜያዊነት ተነሰቶ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ በክብር
ተመልሶ ይተከላል የሚል ምላሽ በመስጠት ተቃውሞውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

 

አንዳንድ የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ሹማምንት የሕዝቡን ተቃውሞ ሐውልት ይሻላል ወይስ የድንጋይ ክምር በማለት እስከማጣጣል መድረሳቸውም የሚታወስ ነው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየቱን ያሰፈረው ወጣቱ ደራሲ በእውቀቱ ስዩም ሀውልቱ ሲነሳ የፈጠረበትን ስሜት ሲገልጽ ” ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ጋዜጠኛ ጓደኞቼ ካሜራቸውን ታጥቀው ደረሱና ተቀላቀሉኝ ሀውልቱን ማስቀረት ስላልቻሉ ምስሉን ቀርጸው ለማስቀረት ተሯሯጡ። ድንገት ቀና ብየ ሳይ ከሀውልቱ ፊት ለፊት ጅማ በር የሚባል ፣ ጣሊያን የሰራው አሮጌ ህንጻ ይታየኛል። ባቡሩ የአቡነ ጴጥሮስን መታሰቢያ ደቅድቆ ሲያልፍ፣ ጣሊያን  ሰራሹን ግንብ ንክች አያደርገውም። ጉደኛ ባቡር” ብሎአል።

 

በእውቀቱ ” አዲስ አበባ ከጊዜ በሁዋላ ያለጥርጥር ባቡር ይኖራታል። ቀለበት መንገዶች ይኖሯታል። አሪፍ ህንጻዎች ይኖሯታል። ነገር ግን ትናንት የሚባል ነገር አይኖራትም።ታሪክ የሌላት ከተማ የሚለው ለአዲስ አበባ የተገባ ቅጽል ነው ሲል አክሎአል።