ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአማራና በሙርሲዎች ላይ የሚደገረውን መፈናቀል በመቃወም እንዲሁም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የቀጠለውን የሰብዓው መብት ረገጣ በማውገዝ በኒውዮርክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽ/ቤት ትናንት የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ።
በሰብዓው መብት ረገጣ የሚጠየቁ ባለሥልጣናት ስም ዝርዝር የያዘ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስገብተዋል።
በተያያዘ ዜና በዊኒፔግ ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መንግሥት በአማራ ተወላጆች ላይ የሚያደርሰውን የማፈናቀል ተግባር በፅኑ አወገዙ:: ማፈናቀሉና እንግልቱ እንዲቆምም ጠየቁ።
በካናዳ ዊኒፔግና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከትላንተ በስቲያ ባደረጉት ስብሰባ እንደገለጡት በአሁኑ ሰዓት መንግሥት በአማራ ተወላጆች ላይ የሚያደርገው ማፈናቀልና ሰብዓዊ መብት ረገጣ አንድን ዘር ከሀገሪቱ አራቱ ማዕዘናት የማፅዳት ተግባር በመሆኑ በፅኑ አውግዘነዋ ብለዋል።
መንግሥት በቤኒንሻንጉል፣ በአርባ ጉጉና በሌሎች ቦታዎች በአማራው ተወላጅ ላይ ላደረሰው ግፍና በደል በዓለም-ዐቀፍ ፍርድ ቤት ሊጠየቅ ይገባል ያሉት የዊኒፔግ ተሳብሳቢዎች ይህን ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
በኢህአዴግ መንግሥት የአማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል ለዓለም ማኅበረሰብ የሚያጋልጥና ሁኔታዎችን የሚከታተል ኮሚቴ በተቋቋመበት በዚህ ስብሰባ በቀጣይነት የካናዳ መንግሥት ተወካዮችና በካናዳ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚሳተፉበት ስብሰባ እንደሚዘጋጅ ምንጮች ከካናዳ አስታውቀዋል።