አንድነት መድረክ በቶሎ ወደ ውህደት እንዲያመራ ጠየቀ

ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመድረክ ስር ያሉ ፓርቲዎች በአስቸኳይ ወደ ውህደት እንዲመጡ አንድነት ለፍትህና ለነፃነት ፓርቲ ጠየቀ።

የ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት  መድረክን የሥራ አፈፃፀም ላለፉት አምስት ወራት ሲገመግም እንደቆየ የገለጸው አንድነት ፓርቲ፤ በመድረክ ስር ያሉ ፓርቲዎች በቶሎ ውህደት እንዲፈጥሩ ነው ጥያቄ ያቀረበው።

የ አንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ሚያዚያ 19 ቀን 2005 ዓመተምህረት ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ በሰጠው ገለፃ፤የ አራት ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው የ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ላለፉት አራት አመታት አሳሳቢ በሆኑ በርካታ ችግሮች ተተብትቦ የቆየ ቢሆንም፤አገሪቱን ወደ ዲሞክራ ያዊ፡ሥርዓት ለማሸጋገር በተደረገው ትግል የተጫዎተው ሚና ከፍ ያለ መሆኑን አውስቷል።

ስብሰባው የተካሄደው፤የመድረክ አጠቃላይ ሁኔታም ብሔራዊ ምክር ቤቱ በሰየመው ኮሚቴ በስድስት ክፍል ተገምግሞ የቀረበውን ሪፖርት በመንተራስ እንደሆነም አንድነት አመልክቷል።

በግምገማ ሪፖርቱ ላይ የተወያየው ብሔራዊ ምክር ቤቱም የመድረክ አባላት የትብብር ጉዞ በውህደት እንዲጠናቀቅ ወስኗል።

በ አሁኑ ጌዜ አገሪቷ እጅግ አሣሳቢ ሁኔታ ላይ በመሆኗ፤መድረክ ራሱን ገምግሞ የ ኢትዮጵያ ህዝብ በሚፈልገው ደረጃ በማጠናከር፣አማራጭ የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ተገቢውን እንቅስቃሴ በማድረግ እና ህዝቡን በዙሪያው በማሰባሰቡ ረገድ የላቀ ጥረት እንዲያደርግ ብሔራዊ ምክር ቤቱ አስገንዝቧል።