ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከትንሣኤ በኋላ በርካታ የአማራ ተወላጅ የሆኑ መናኞች እንዲወጡ ታዘዋል።
በዋልድባ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አባት ዛሬ ከኢሳት ጋር በተለይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጡት በገዳሙ ነዋሪ የነበሩ መናኝን የመንግሥት ታጣቂዎች ከማይፀምሪ መጥተው እንደወሰዷቸው የገለፁ ሲሆን በመሀል መንገድ አውርደው ከደበደቡና ከፍተኛ ጉዳት ካደረሱባቸው በኋላ ያላቸውን ገንዘብና ሰነድ እንደዘረፏቸው አረጋግጠዋል።
በዋልድባ የሚገኙ መናኞችና አባቶች የቤተክርስቲያንና የሃገር ቅርስን ለመከላከል፣ ገዳሙን ከጥፋት ለመታደግ የሚችሉትን ጥረት አድርገዋል ያሉት አባት በዚህ ጥረትም ተደብድበናል ተሰደናል ከዚህ በኋላ ምዕመናኑ ኃላፊነቱን ይረከብ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የገዳሙ ንብረትና ቅርስ ከዘረፋ የመከላከል ጉዳይ ከአባቶች አቅም በላይ መሆኑን የሚያመለክቱት አባት በባንክ ያለው ገንዘብ ቀድሞ ጎንደር ነበር አሁን ግን ወደ ሽሬ ተዛውሯል ብለዋል።