የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተፈጥሯዊ ደን በእሳት መያያዙ ተዘገበ

ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሰደድ እሳቱ ከተነሳ 3ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን የደባርቅ አካባቢ ሕዝብ ያደረገው ጥረት እሳቱን ሊያጠፋው አልቻለም።

ዛሬ ኢሳት ያናገራቸው የደባርቅ አካባቢ ነዋሪ እንደገለጡልን ብርቅና ድንቅ አዕዋፍ፣ እንስሳትና ዕፅዋትን ያቀፈው የስሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ ከክልልና ከፌዴራል እሳት አደጋ መከላከያ እገዛ ካልተደረገ ከፍተኛ አደጋ ላይ ይገኛል።

በሳንቃ በር አካባቢ በሚገኘው የፓርኩ ክፍል የተነሳው እሳት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትንና (በሌላው ዓለም የማይገኙትን)እንደ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ዋልያ ቀይ ቀበሮና ሌሎችንም ብርቅና ድንቅ እንስሳት አዕዋፍና ዕፅዋት እያቃጠለ እንደሚገኝ የገለፁት ኢሳት ያናገራቸው በደባርቅ አካባቢ ነዋሪ፣ የሚመለከተው አካል እሳቱን የማጥፋት ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ራስ ዳሸንን ጨምሮ ትላልቅ 17 ተራሮችን ያቀፈው የሰሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረበና አደጋ ላይ ያሉ ተብለው በዩኔስኮ የተቀመጡ እንስሣት፣ እፅዋትና አዕዋፍ መኖሪያ ያደረገ ፓርክ መሆኑ ይታወቃል።