በጋምቤላ ክልል የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላትን ጨምሮ በ23 ሰዎች ግድያ የተከሰሱ ሞት ተፈረደባቸው

ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፌዴራል ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ በ23 ሰዎች ግድያ የከሰሳቸው ዘጠኝ ሰዎች ሲሆኑ ሶስቱ በተገኙበት ስድስቱ ላይ ደግሞ ባልተገኙበት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል:: በሌሎቹ ላይ ደግሞ ከ21 እስከ 9 ዓመት የሚደርስ እስር ወስኖባቸዋል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ ማመልከቻ እንደሚያብራራው ኡመድ ኡከት የተባለው ፍርደኛ ከግብረ አበሮቹ ጋር በአኙዋክ ዞን አበቦ ወረዳ ድቦንግ ቀበሌ ነዋሪ የነበረውን ዋሪ ኡመድ የተባለውን የመከላከያ ሚኒስቴር ተጠባባቂ ኃይል በጥይት ደብድቦ ገሏል ይላል።

በተመሳሳይም በኬላ ጥበቃ ላይ የነበሩ የክልሉ ፖሊስ ልዩ ኃይል ባልደረቦች ምክትል ኢንስፔክተር ኦባንግ ኦሣው እንዲሁም ረዳት ሳጅን ኦፕና ኡጁሉ በጥይት ደብድቦ መግደሉን ይኀው የዐቃቢ ሕግ የክስ ማመልከቻን የጠቀሰው ሪፖርተር ዘግቧል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሞት ፍርድ እንዲቀጡ የወሰነባቸው በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በሚገኙት ኡመድ ኡከት፣ ኡመድ ኡጁሉ፣ ገመቹ ፖል ኡመድና በሌሉበት ጉዳያቸው ሲታይ የቆዩት ኡመድ ኤዴል፣ ኡጁሉ ባብ ኡባንግ ኪሩ፣ ኡራንግ ኡቻን፣ ኪሩ ኡመድና አካይ ኦፒዮ ናቸው።

በ2004 ዓ.ም. በ17 ተማሪዎች ላይ በተደረገው ግድያ ጭምር ከተከሰሱትና በሞት ከተቀጡት ከነዚህ ሰዎች በተጨማሪ በኡመድ ኡመድ ኪሩ ኡመድ ኡኮችና አዱኛ ኡማን እያንዳንዳቸው በ21 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲሁም በዋና ሳጅን ኦኬሎ ኡጁሉና ኦዋፕንግ ኡሌንግ እያንዳንዳቸው በዘጠኝ ዓመት እስር እንዲቀጡ፤ ሁሉም በእስር የተቀጡት ለአምስት ዓመታት ሕዝባዊ መብታቸው እንዲነሳም ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

በተለይ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ተከሳሾች ራሱን የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ የተባለ ድርጅት አባል መሆናቸውን ያመለከተው የክስ ማመልከቻ በዚህ ድርጅት ጥላ ሥር ሆነው በርካታ የሽብር ተግባራት ፈፅመዋል ይላል