ሚያዚያ ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዋሳ ዩኒቨርስቲ ስር የሚገኘው የወንዶገነት የደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር ጸጋየ በቀለ እና የኮሌጁ የፖሊስ ክፍል አዛዥ ሻምበል አለማየሁ ወረታ የታሰሩት የመንግስት ባለስልጣናት የኮሌጁን መሬት በመቁረጥ ለአካባቢው ተወላጅ ባለሀብት ለመስጠት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመቃወማቸው ነው።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ዩኒቨርስቲው ባለስልጣን ለኢሳት እንደገለጹት ሁለቱም ግለሰቦች የታሰሩት የአካባቢው ባለስልጣናትየኮሌጁን መሬት በመውሰድ ለአንድ ባለሀብት ለመስጠት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ሁለቱ ሰዎች አጥብቀው በመቃወማቸው ነው።
ሻምበል አለማየሁም ሆኑ ዶ/ር ጸጋየ “መሬቱ የኮሌጁ በመሆኑ ፈርመን አንሰጥም” በማለታቸው ካለፈው አረብ ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆኑ፣ ባለስልጣኑ እንደሚሉት ጉዳዩ ከዘር ጋር የተያያዘ ነው። ሻምበል አለማየሁ የሲዳማን ህዝብ ለመውጋት ጦር አዘጋጅተዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ እሳቸውን ለመያዝ ከ12 በላይ ፖሊሶች ወደ ዩኒቨርስቲው ሲገቡ መጠነኛ ረብሻ ተነስቶ እንደነበርም ለማወቅ ተችሎአል። ሻምበል አለማየሁ በተያዙበት ወቅት ” ወንጀል አልፈጸምኩም ወንጀሌ አማራ መሆኔ ብቻ ነው” በማለት ይናገሩ እንደነበር የአይን እማኞች ተናግረዋል። ወንዶገነት
በጉዳዩ ዙሪያ የአካባቢውን ባለስልጣናትን ለማነጋገር አደረግነው ሙከራ አልተሳካም።