ሚያዚያ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቤንሻንጉል ጉሙዝ በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን መፈናቀል ለማጣራት ወደ መተከል ዞን አቅንተው የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ የፓርቲው ም/ል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳና የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በቃሉ አዳነ በቡለን ወረዳ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢሳት በሰበር ዜናው ካቀረበ በሁዋላ ፣ ሶስቱም አመራሮች ማምሻውን ተለቀዋል።
አመራሮቹ የታሰሩት ከፌደራል መንግስት፣ ከክልል መንግስት እና ከዞን ባለስልጣናት ወደ ወረዳው ገብተው ሰዎችን ለማነጋገር የሚችሉበትን የፈቃድ ወረቀት ይዛችሁ አልመጣችሁም ተብለው መሆኑን ምህረት ተደርጎላቸው ከእስር ተፈተው ወደ አዲስ አበባ በበመለስ ላይ ያሉት ሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል::
ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ያለፈቃድ ሄዶ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ለመነጋገር አይቻልም፣ በዚያ ላይ እናንተ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ናችሁ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ኢ/ር ይልቃል ፣ እንዲህ አይነት ስራ ለመስራት በቅድሚያ ከክልል ፣ ከዞንና ከወረዳ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ፣ ይህን አለማድረግ ደግሞ የብሄረሰቦችን የራስን በራስ የማስተዳደር መብት መናቅ ተደርጎ እንደሚታይ እንደተነገራቸው ገልጸዋል። ኢ/ር ይልቃል ከሚመለከታቸው አካላት ህጋዊ ፈቃድ መያዛቸውን ገልጸው ዋናው አላማቸው ጉዳቸው እንዳይወጣ በመፍራት መሆኑን ገልጸዋል።
አንዳንድ ሰዎችን በማናገር ያዘጋጁት ቪዲዮ በወረዳው ባለስልጣናት ትእዛዝ እንዲደመሰስ መደረጉን ኢንጂነሩ ተናግረው ይሁን እንጅ በአይናቸው ያዩት፣ በጆሮዋቸው የሰሙት በቂ መረጃ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።
መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን እና እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ለመሸፋፈን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። የመንግስት ባለስልጣናት የወሰዱት እርምጃ የመንግስት ባለስልጣናትን በአለማቀፍ ፍርድ ቤት በዘር ማጥራት ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን አለማቀፉ የህግ ምሁር ዶ/ር ያእቆብ ሃይለማርያም መናገራቸው ይታወሳል።