የካቲት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ላለፉት 21 አመታት ኢትዮጵያን በምግብ እራሱዋን እንደሚያስችል ቃል ሲገባ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት በቅርቡ ከውጭ የተገዛውን 850 ሺ ኩንታል ስንዴ እንደሚያስገባ የእህል ንግድ ድርጅት አስታውቋል።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም 5 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ አስገብቶ ማከፋፈሉን የገለጠ ሲሆን፣ የስንዴው መግባትም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የእህል ዋጋ ንረት ለማለዘብ እንደረዳ ድርጅቱ አስታውቋል።
መንግስት በአሁኑ ጊዜ በግብርናው ዘርፍ ያለው ምርታማነት የአገሪቱን ህዝብ በበቂ ሁኔታ ሊመግብ ባለመቻሉ፣ ስንዴ ከውጭ እየገዛ ለማከፋፈል ተገዷል። ለብዙዎች እንቆቅልሽ የሆነው የህንድ እና የሼክ አላሙዲን ኩባንያዎች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በመውሰድ ሩዝ እያመረቱ ወደ ህንድና ሳውዲ አረብያ ቢልኩም፣ ኢትዮጵያ ግን አሁንም እህል ከውጭ አገራት ከመግዛት አላመለጠችም።