ከአርቲስት ታምራት ሞላ ቀብር ጋር በተያያዘ ቅሬታ ቀረበ

የካቲት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ እንደ ቅርስ ከሚታወቁት አንጋፋ ድምፃውያን አንዱ የሆነው አርቲስት ታምራት ሞላ የምድር ጦር ሰራዊት ኦኬስትራ ማርሽ ሊዘጋጅለት ይገባ ነበር ሲል ሌላው አንጋፋ አርቲስት ዳምጠው አየለ ቅሬታውን ገለጠ።

አርቲስት ዳምጠው እርሱ በሚቀጠርበት ጊዜ የሙያ ገምጋሚው አርቲስት ታምራት እንደነበር ገልጾ፣ ለ30 አመታት ያክል ሳይለያዩ በምድር ጦር አገልግሎት መስጠታቸውን አውስቷል።

እኛ የምንሰራው ለአገር፣ ለሙያ ፍቅር እንጅ ለሌላ አልነበረም ያለው አርቲስት ዳምጠው፣ አርቲስት ታምራት ሞላ ኩሩ፣ ሽቅርቅር ፣ ንጹህ እና ከሰዎች ጋር መኖር የሚችል ነበር ብሎአል ።

ምድር ጦርን ምድር ጦር ካሰኙት አርቲስቶች መካከል ታምራት አንዱ መሆኑን የገለጠው አርቲስት ዳምጣው፣ የመከላከያ ሙዚቃ ክፍል ቢያንስ የሀዘን ማርሽ ለማሰማት አለመቻላቸው እንዳሳዘነው ገልጧል።

የአርቲስት ታምራት የቀብር ስነስርአት በትናንትናው እለት በቅድስት ስላሴ ካቴደራል ተፈጽሟል።