የካቲት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ወንጀል ችሎት በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና በአሳታሚው ድርጅት በማስተዋል የህትመትና የማስታወቂያ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ በአቶ ማስ ተዋል ብርሀኑ ላይ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል።
የችሎቱ ዳኛ አቶ አይሸሹ ሽመልስ ውሳኔያቸውን በንባብ ያሰሙ ሲሆን የፌደራል አቃቢ ህግ ያቀረባቸውን 4 ክሶች በንባብ በማሰማት ፣ ሙሉ በሙሉ የአቃቢ ህግን ክስ ያለምንም ማብራሪያ በመቀበል የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ አቶ አምሀ መኮንን ክሱን እንደሚከላከሉ ለችሎቱ ገልጠው የመከላከያ ምስክር ለማቅረብ ፣ ምስክሮቹ በውጭም የሚገኙ ስላሉ እና በደንበኛየ ላይ የቀረበው ክስ ከፍተኛ ስለሆነ በአግባቡ አዋቅሮ ለማቅረብ ረዘም ያለ ጊዜ ቀጠሮ ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል።
ዳኛው አቶ አይሸሹም በሚዲያ ላይ የሚቀርብ ክስ በአጭር ቀጠሮ እንዲጠናቀቅ ህጉ የሚደነግግ በመሆኑ ቀጠሮው ለመጋቢት 17 ቀን 2005 ዓም ከቀኑ ሶስት ሰአት ላይ እንዲሆን ውሳኔ አስተላልፈዋል።
ችሎቱን፣ የጋዜጠኛው አድናቂዎች፣ የውጭ ዲፕሎማቶች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተማጓቾችና ቤተሰቦች ተገኝተው ታዝበዋል።