ኢሳት ዜና
የራሽ ደጀን ተራራ በሚገኝበት በሏሪ ቀበሌ በበዬዳ ወረዳ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችን፣ በትግራይ ክልል ውስጥ እንዲካተቱ ለማሳመን ለ7 ተከታታይ ቀናት የተደረገው ውይይት ሳይሳካ መቅረቱን ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጠዋል።
የትግራይ ክልል ባለስልጣናት የቀበሌው ነዋሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲዛወሩ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም፣ ህዝቡ ግን እና በታሪክ ተወቃሽ አንሆንም፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን አጥንታቸው የተቀበረው በዚሁ ቦታ ነው። ግዛቱ ማን እንደሆነ ይታወቃል። በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
ከዚህ ቀደም ራስ ደጀን ተራራ በትግራይ ክልል ይገኛል በማለት በመጽሀፍ መልክ ታትሞ መቅረቡን እንዲሁም ላለፉት ተከታታይ አመታት የራስ ደጀን አካባቢን ህዝብ ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት ተደጋጋሚ ሙከራ መደረጉን ያስታወሱት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ግፊት ከዚህ በፊት ከታየውም የባሰ ነው ይላሉ።
ትግራይ አካባቢውን ለመውሰድ ለምን እንደፈለገ የተጠየቁት ነዋሪዎቹ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው ለቆርቆሮና ለተለያዩ እቃዎች መስሪያ የሚሆን ከፍተኛ ማእድን በመገኘቱ ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን አስፍረዋል።
የአካባቢው ወጣቶች የትግራይ ክልል እየፈጸመ ያለውን ተግባር በእጅጉ እየተቃወሙት ነው።
በየዳ አካባቢ ህዝብ ሙሉ በሙሉ አማርኛ ተናጋሪና በታሪክም የጎንደር ግዛት መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
እስካሁን አካባቢውን በጉልበት ለመከለል ጥረት አለመደረጉን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ አሁን የሚታው ሁኔታ ከቀጠለ በአካባቢው ግጭት ሊነሳ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ራስ ደጀን ተራራ በትግራይ ክልል ይገኛል ተብሎ በእንግሊዝኛ መጽሀፍ ውስጥ መስፈሩን በማስመልከት የክልሉ መንግስት በስህተት የተፈጸመ ነው ቢልም፣ እስካሁን ለማስተካከል ሙከራ አለመደረጉን ታዛቢዎች ይናገራሉ።
በየዳ ወራደ ቀድሞ በደባርቅ አውራጃ ውስጥ ይገኝ እንደነበር ይታወቃል።
አንዳንድ ወገኖች ራስደጀን ተራራም ሆነ በዙሪያው ያለው መሬትም ሆነ ማእድን የኢትዮጵያ ህዝብ ሆኖ እያለ፣ አላስፈላጊ የሆነ የባለቤትነት ጥያቄ በማንሳት ህዝቡ እንዲከፋፈል በማድረግ ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ ነው ይላሉ።