ስር እየሰደደ በመሄድ ላይ ስላለዉ የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ረገጣ የተነጋገረ ሕዝባዊ ስብሰባ በለንደን ተካሄደ።

ኢሳት ዜና:- የመለስ መንግሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፋ ደረጃ በህዝብ ላይ በሚፈፅመዉ የሰብኣዊ መብት ረገጣ ላይ የተነጋገረዉ ታላቅ ሀዝባዊ ስብሰባ የተካሄደዉ በለንደን ፍሬንድ ሃዉስ አዳራሽ ሲሆን ቁጥራቸዉ በሁለት መቶዎች የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተዋል።

ስብሰባዉን በንግግር የከፈቱት የ3ኛዉ አለም የሁሉም የፓርላማ ቡድኖች ህብረት ሊቀመንበር የተከበሩ ካዉንስለር ሙሽራክ ላሺር ናቸዉ።
ካዉንስለሩ በመክፈቻ ንግግራቸዉ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ የሰብኣዊ መብት አያያዝ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ በመግለፅ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ምክንያት የሶስተኛዉ አለም ህብረት የፓርላማ ቡድን ከኢትዮጵያ የዲሞክራሲና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በመተባበር ሁለት የህዝብ ስብሰባዎች ማካሄዱን ገልፀዋል።

ካውንስለር ሙሽራክ ላስር በኢትዮጵያ ዉስጥ ገንዘብና ስልጣን ከፍተኛ የሆነ ሙስናን ብሎም የሰብኣዊ መብት ረገጣን ሊያስከትሉ እንደቻሉ ገልጠው፣ ሕዝብ በረሃብና በድህነት በሚሰቃይባት አገር ጠ/ሚኒስትሩና ደጋፊዎቻቸዉ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በዉጭ አገር በማካበት ላይ እንዳሉና የምእራቡም አለም “በፀረ ሽብር ተባባሪነት” ስም በህዝብ ላይ የሚደርሰዉን የመብት ጥሰት ችላ እንዳለዉ አክለዋል።

በመክፈቻ ንግግራቸዉ ማጠቃለያ ላይ ኢትዮጵያዊያን ህብረት ፈጥረዉ በጋራ መንቀሳቀሳቸዉ፤ በለንደን በሚገኙት በፓርላማ ተወካዮቻቸዉ አማካይነት በህዝብ ላይ የሚደርሰዉን ግፍና ስቃይ የብሪታኒያ መንግስት ይበልጥ እንዲረዳዉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ በመጪዉ ነሃሴ ወር ዉስጥ በኢትዮጵያ ምርጫን በተመለከተ በፓርላማ ዉስጥ የሚስተናገድ ሕዝባዊ ስብሰባ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

ማስ አድቮኬሲ ፎር ሂዩማን ራይት ኢን ኢትዮጵያ የተባለዉ ቡድን ባዘጋጀዉ ይኸዉ ለአራት ሰዓታት በተካሄደዉ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት በቅርቡ ኢንቬስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም ቢሮ ከቢቢሲ ኒዉስ ናይት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለድሃዉ ህብረተሰብ የሚሰጠዉ የዉጭ ርዳታ የገዢዉ ፓርቲ/ህወሃት/ የፖለቲካ መጨቆኛ መሳሪያ መሆኑን ያጋለጡት ጋዜጠኛ አንገስ ስቲክለር ነበሩ።

መለስና ፓርቲያቸዉ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ብሪታኒያን ጨምሮ ከምእራቡ አለም በገፍ እየተቀበሉ የኢህአዴግ ደጋፊ ያልሆኑትን ለማጥቃትና በረሃብ ለመቅጣት በፖለቲካ መሳሪያነት እየተጠቀሙበት እንዳለ ያጋለጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለዉለታ በመሆናቸዉ ተሰብሳቢዉ ለጋዜጠኛ አንገስ ስቲክለር ያለዉን አድናቆት በከፍተኛ ጭብጨባ ገልጾላቸዋል።
እሳቸዉና ባልደረቦቻቸዉ ያጠናቀሩትን መረጃ የኢትዮጵያ መንግሰት አምኖ አለመቀበሉ የሚጠብቁት ነገር እንደሆነ የገለፁት ጋዜጠኛ አንገስ፣ በየገጠሩ ተዘዋዉረዉ ያገኙት ማስረጃ በእጃቸዉ እንዳለና በሰሩት ስራ ሙሉ እምነት እንዳላቸዉ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛ አንገስ በተዘዋወሩባቸዉ መንደሮችና ሰፈሮች ዉስጥ መረጃ የሰጧቸዉን ድሃ ገበሬዎች የመለስ መንግስት የፀጥታ ሃይሎችን በማሰማራት፤ በማሰስና በማፈላለግ በንፁሃን ዜጎቹ ላይ ያደረሰባቸዉ ወከባና እንግልት እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ አልሸሸጉም።

የኢትዮጵያ መንግስት በኦጋዴን ሶማሌ ክልል በህዝብ ላይ የሚፈፅመዉን የሰብኣዊ መብት ጥሰት ለመከታተል በሚስጢር የገቡትን ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞችና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን በሽብርተኝነት እንዳሰራቸዉና ክስ እንደመሰረተባቸዉ አንገስ አስታዉሰዉ፣ በህግ ወንጀለኛነታቸዉ ሳይረጋገጥ ጠ/ሚር መለስ ሽብርተኞች ናቸዉ በማለት ፍርድ መስጠታቸዉን አመልክተዋል።

የኢንቬስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም ቢሮ የብሪታኒያ መንግስት የሚሰጠዉ የርዳታ ገንዘብ ለተረጂዎች ላለመድረሱ አሳማኝ ማስረጃ እያለ የአለም አቀፍ የዉጭ ርዳታ የካቢኔ ሚኒስትር አንድሪዉ ሚቼል ስለጉዳዩ ለማሰተባበል ያደረጉት ጥረት ወይ ባለማወቅ ወይ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ክህደት መሆኑን በመጥቀስ፣ ግብር ከፋዩ የብሪታኒያ ህዝብ እዉነቱን ማወቅ መብቱ እንደሆነ በማመን ድርጅታቸዉ የሚኒስትሩን ማስተባበያ በቀላሉ እንደማይመለከተዉና ሌሎች ተጨማሪ ጥያቄዎች መነሳታቸዉን አስረድተዋል።

የብሪታኒያ ህዝብ በሚከፍለዉ ግብር ይህን መሰል ተግባር እንዲፈፀምና እንዲህ ያሉ የካቢኔ ሚኒስትር እንዲህ ብለው መናገር እንደማይገባቸው ጋዜጠኛ አንገስ ተናግረዋል።
በማያያዝም በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ያለዉ የሰብኣዊ መብት ረገጣ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ራፖርተር ጥያቄ መቅረቡንና ራፖርተሩም እንዲጣራ አምኖ ጥያቄዉን መቀበሉን አስረድተዋል።

የሰብሰባዉን መድረክ ከሌሎች ጋር በአወያይነት የመሩት ታዋቂዉ የቢቢሲ የፖለቲካ ገምጋሚ፤ ሃያሲና ፀሃፊ የሆኑት ዶ/ር ቪንሰንት መኮምቤ ፣ እንደቢቢሲ ያሉ የዜና ማሰራጫዎች፣ የራሳቸዉን አገር ዩጋንዳን ጨምሮ የምእራብ መንግስታት ለራሳቸዉ ፍላጎት ሲሉ ከአምባገነን የአፍሪቃ መሪዎች ጋር የሚፈጥሩትን ግንኙነት አጥብቆ መዋጋት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተሰብሳቢዎች ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉባቸዉ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበዉ ጋዜጠኛ አንገስና አዘጋጆቹ መልስ የሰጡባቸዉ ሲሆን በኢትዮጵያ በተለይም በኦጋዴን ክልል በመካሄድ ላይ ያለዉን ዘግናኝ የሰብኣዊ መብት ረገጣ፤ ሰቆቃና ወከባ የሚያሳይ ዶኩሜንታሪ ፊልም ለተሰብሳቢዉ እይታ መቅረቡን ንጉሴ ጋማ ዘግቧል።