ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ለሞት፤ ለእስራትና ለሰቆቃ ሲዳርግ የነበረዉ የቀድሞዉ የህወሃት/ኢህአዴግ የደህንነት ባለስልጣን ለፍርድ ሊቀርብ እንደሚችል ተገለፀ

ኢሳት ዜና:- የቀድሞዉ የህወሃት የደህንነት ሹም የነበረዉና በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ኮለምበስ ኦሃዮ ነዋሪ በመሆን ለኢህአዴግ መንግስት የስለላና የመረጃ ስራ የሚያከናዉነዉ ብስራት አማረ የተባለዉን ግለሰብ ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችል ስራ በመሰራት ላይ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ደምሴ በላቸዉ የተባሉ የኮሎምበስ ነዋሪ ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሬዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ግለሰቡ በ2002 በዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቆ በተቃዋሚ ጎራ የቆመ በማስመሰል ገፅታዉን ካሳየ በሁዋላ በኢህአዴግ አማካይነት ከኢትዮጵያ ዘርፎ በመጣዉ ገንዘብ የንግድ ድርጅት ከፍቶ በኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎችን እንደሚሰልል ገልፀዋል።

የቀድሞዉ የህወሃት አባል የነበሩት ገብረ መድህን አርአያ ከአዉስትራሊያ በቅርቡ “ብስራት ማነዉ? አየጥ ሞቷን ስትሻ…” በሚል ርእስ ባሰራጩት ፅሁፍ ብስራት አማረና የህወሃት የደህንነት ሰዎች የበርካታ ንፁሃን ዜጎችን ደም እንዳፈሰሱና የአካልና የአእምሮ ስብራት እንዳደረሱ ማጋለጣቸዉ ይታወሳል።

በቀድሞዉ መንግሰት ዉስጥ የቀይ ሽብር ወንጀለኛ የነበረዉ ቀልቤሳ ነገዎ ከዚሁ ከአትላንታ ኦሃዮ ለመለስ መንግስት ተላልፎ የተሰጠ መሆኑን በማስታወስ ብስራት አማረን በሚመለከት ለመለስ መንግሰት ተላልፎ ቢሰጥ እንዲያዉም ተሹሞ ሌሎች ወንጀሎችን ከመፈፀም ወደሁዋላ ስለማይመለስ ግብረ ሃይሉ በመስራት ላይ ያለዉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ሳይሆን በዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ በእስር ቤት እድሜዉን እንዲያሳልፍ መሆኑ በቃለ ምልልሱ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ይኸዉ ብሥራት አማረ የተባለዉ ግለሰብ የቀድሞው የሕወሓት መሥራች ና የዓረና አመራር አባል የሆኑትን አቶ አስገደ ገብረ ሥላሴን “ጋሃዲ 3” በሚለው መጽሐፍ ላይ በትግል ወቅት በነበረው ሐላፊነት ሰዎችን በእሳት በመግረፍ፣ በማሰቃየት እና በመደብደብ ምርምራ ያካሂድ ነበር በማለት እንደፃፉበት በመግለፅ ክስ የመሰረተባቸዉ መሆኑ ታዉቋል።

አቶ አስገደ በቀረበባቸዉ ክስ ምላሽ ለመስጠት ለጥቅምት 14/2004 ቀጠሮ የተሰጣቸዉ ሲሆን ይኸዉ በተለያዩ የቀድሞ የህወሃት አባላት ስለብስራት አማረ የሚሰጠዉ አስተያየት በዩናይትድ ስቴትስ ለሚመሰረትበት ክስ ተጨማሪ ማስረጃ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ታዛቢዎች ይናገራሉ።