ታህሳስ ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከስቶ የነበረውን የብሄር ግጭት ተከትሎ ከ100 በላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መታሰራቸውን የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ሊግ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ታስረዋል ያላቸውን የ99 ተማሪዎች ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገው የሰብአዊ መብት ድርጅቱ አብዛኞቹ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ጠቁሟል።
ከታሰሩት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የኦሮሞ ተወላጆች ቢሆንም፣ የአማራና የትግራይ ተማሪዎችም ይገኙበታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይንስ ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው ብሄር ተኮር ግጭት መንግስት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በባህርዳር ከተማ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ተረጋግጧል በማለት በእየአመቱ የሚያከብረውን የብሄረሰቦች ቀን ባከበረ ወር ባልሞላው ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ ነው።