ባለሀብቶች ለኢህአዴግ ጽ/ቤት ግንባታ ቃል የገቡትን ገንዘብ ሊሰጡ አልቻሉም ተባለ

ታህሳስ  ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዚህም ምክንያት  የግንባሩ ጽህፈት ቤት ግንባታ መስተጓጎሉን ሪፖርተር ዘግቧል።

ጋዜጣው እንዳለው ከአራት ዓመት በፊት ኢሕአዴግ ሰባት ፎቅ ከፍታ ያለው ሕንፃና ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰንዳፋ ከተማ የካድሬዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመገንባት ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡

አራት ኪሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አካባቢ ይገነባል የተባለው የኢሕአዴግ ፖለቲካ የሚቀመርበት ዋና መሥርያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ቢስተጓጎልም፣ እስካሁን ድረስ በተገኘው ገንዘብ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር በሚወስደው መንገድ ላይ በኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ከተማ የካድሬዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት እየተገነባ ይገኛል፡፡
በወቅቱ ለ እነዚህ ግንባታዎች 130 ሚሊዮን ብር እንደሚፈልግ የተገለፀ ሲሆን፤ የግንባታዎቹን ዲዛይን በነፃ የሠሩት ኤምኤች ኢንጂነሪንግና አልቲሜት ፕላን ኩባንያዎች ናቸው፡፡

ያንንም ተከትሎ  የአገሪቱ ታላላቅ ባለሀብቶች  ፕሮጀክቱን ፋይናንስ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውና ቃል ገብተው እንደነበር ተመልክቷል።

በአስመጪና ላኪ ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ፣ በኮንስትራክሽንና በሌሎች ዘርፎች   የተሰማሩ ባለሀብቶች እያንዳንዳቸው ከመቶ ሺሕ ብር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ለመለገስ ነበር ቃል የገቡት፡፡

ይሁንና  ከአራት ዓመት በኋላ ከባለሀብቶቹ መካከል የተወሰኑት ቃል የገቡትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ አላስገቡም ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በመጪው መጋቢት ወር በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የኢሕአዴግ ዘጠነኛው ጉባዔ ላይ በእነዚህ ጉዳዮች ዙርያ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሁለቱንም ግንባታዎች በአንድ ወቅት ለማስጀመር ዕቅድ ይዞ የነበረው ኢሕአዴግ፣ ሙሉ ለሙሉ ገንዘቡን ባለማግኘቱ ባገኘው ገንዘብ የካድሬዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ላይ ብቻ ትኩረት ለማድረግ መገደዱንም  ምንጮቹ ጨምረው  ገልጸዋል፡፡

ይህ ትምህርት ቤት ቀደም ሲል በሰንዳፋ -በኬ ከተማ እንደሚገነባ የተያዘው  ዕቅድ ተሰርዞ ነው በሱልሉታ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው፡፡