የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ዘንድ እየተከበረ ነው

ታህሳስ  ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በየአመቱ ታህሳስ 29 የሚከበረው የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በአል በመላው የኢትዮጵያ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ሲሆን በአገሪቱ የሚታየው የኑሮ ውድነት የበአሉን ድምቀት እንደቀነሰው ምእመናን ተናግረዋል።

ዘጋቢያችን ያነጋገራት አንድ የኦሮቶዶክስ እምነት ተከታይ ቤተክርስቲያኑዋ ከሁለት በመከፈሉዋና የቤተክርስቲያን አባቶች ችግሩን ለመፍታት ባለመቻላቸው ማዘኑዋን ገልጻለች።

በበአሉ ዋዜማ በተደረገው የጸሎት ስነስርአት ላይ እግዚአብሄር ቤተክርስቲያኑዋን እንዲጎበኝ ስትጸልይ ማደሯንም ተናግራለች።

ሌላ የኦሮቶዶክስ እምነት ተከታይ በበኩሉ የዶሮና የበግ ዋጋ ከአምናው ጋር ሲተያይ መጠነኛ ቅናሽ ቢያሳይም፣ በሌሎች እቃዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በበአሉ ድምቀት ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ብሎአል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ የበአል ስሜት እየጠፋ መምጣቱ ሲዘገብ ቆይቷል።