የሺ ጋብቻ ቅዳሜ ይከናወናል

ህዳር ፰ (ሰምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኤሚነንስ ሶሻል ኢንተርፐርነርስ በኢትዮጽያ በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ፤መመዝገቡ የማይቀር ነው ያለውን የአንድ ሺ ጥንዶች ጋብቻ ቅዳሜ ህዳር 8 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስአበባ ጎተራ ማሳለጫ የብሄር ብሄረሰቦች መንደር ተብሎ በሚታወቀው ሜዳ ላይ እንደሚያከናውን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጽያ በዚህ ደረጃና ዓይነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጥንዶች በአንድነት ሲዳሩ የመጀመሪያው ሲሆን ሥነሥርዓቱም ሁሉም ተጋቢዎች የመጡበትን አካባቢ ወይም ክልል ባህል፣አለባበስ በሚያንጸባርቅ መልኩ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡
የጋብቻ ሥነሥርዓቱ የሙሸሮችን ጊዜና ገንዘብ ከመቆጠቡም ባሻገር የብሄር ብሄረሰቦች የጋብቻ ባህል የሚያስተዋውቅና አቀራረቡም በአስደናቂ ትዕይንቶች የታጀበ በመሆኑ ሥነሥርዓቱ በዓለምድንቃድንቅ መዝገብ ለማስመዝገብ ዝግጅት መደረጉን አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ እጅግ በጣም ትልቅ የተባለ ባህላዊ ድፎ ዳቦ ከሚቀርቡት አስደናቂ ነገሮች አንዱ እንደሚሆን ተገልጾአል፡፡