የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ተገቢውን ዕውቅና እየሰጡ አይደለም ተባለ

ህዳር ፰ (ሰምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አቶ መለስ ዜናዊ  ከዚህ ዓለም በሞት ከተሰናበቱ ወዲህ ሕዝቡ ሐዘኑን ከመግለጹ ጋር
ተያይዞ “የመለስን ራዕይ ሳይበረዝ፣ሳይከለስ እናስፈጽማለን” ወደሚል ቅዥት ውስጥ መገባቱን የሚያስታውሱት ዘጋቢያችን የናጋገራቸው ባለሙያዎች ይህንን አጀንዳም እንደ ኢትዮጽያ ቴሌቪዥን ያሉ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ክፉኛ እያራገቡት፣በአንጻሩ ደግሞ አዲሱ
ጠ/ሚኒስትር መኖራቸው እንኳን እየተረሳ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
“የኢትዮጵያን ህዳሴ እናበስራለን” የሚለው ኢቲቪ በአሁን ሰዓት ወሬው ሁሉ “የመለስ ራዕይን እንስፈጽማለን”
ወደ ሚል ዜማ ከመቀየሩም በተጨማሪም የዜና ክፍሉ የኃላ ምስልም(ባክግራውንድ) በአቶ መለስ ፎቶግራፍ አሸብሮቆ
እስካሁን መቀጠሉ ግራ የሚያጋባ ነው ብለዋል፡፡

የትግራይ እና የአማራ ክልሎች ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ተመሳሳይ አቅጣጫን የሚከተሉ ሲሆን ከመቀሌ የሚተላለፈው የትግርኛ ፕሮግራም እስካሁንም በጠ/ሚኒስትሩ ሞት የሚያለቅሱ ሰዎችን ጭምር በተደጋጋሚ እያቀረበ መሆኑ ምን እየተሰራ እንደሆነ ግራ እንደሚያጋባ ጠቅሰዋል፡፡
አንድ ሰማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የመገናኛ ብዙሃኑ ድርጊት አጋጣሚ ሳይሆን ሆን ተብሎ
ታቅዶበት፣ከገዥው ፓርቲም አቅጣጫ ተሰጥቶ የሚሰራበት መሆኑን በማስታወስ፣  ሁኔታው አዲሱን ጠ/ሚኒስትር ተገቢውን
ዕውቅና ላለመስጠት የሚደረግ ብቻም ሳይሆን በጠ/ሚኒስትሩም ላይ አሉታዊ የስነልቦና ጫና የሚያሳርፍና የሚያሸማቅቅ
ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሌላው አስተያየት አጪ በበኩላቸው የአቶ መለስ ሞት በይፋ ከተሰማ ሶስተኛ ወር እየተቃረበ መሆኑን በማስታወስ
ይህን ያህል ጊዜ ሚዲያው ትኩረቱ ሁሉ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ላይ ማድረጉ፣“የእሳቸውን ራዕይ እናሳካለን” እያሉ
በአደባባይ ለሚናገሩት ሁሉ የሚያሳፍር ነው ብለዋል፡፡

ፕሮፓጋንዳው ሕዝቡን ከማሰልቸቱም በላይ ለአዲሱ ጠ/ሚኒስትርም ዕውቅና የመንፈግ ስልታዊ አካሄድ አስመስሎታል
ሲሉ ሒደቱን ተችተውታል፡፡

አንዳንድ ወገኖች ለኢሳት በሚሰጡት አስተያየት ” በፎቶ መገዛት በቃን፣ ፎቶዎችን እንዲያነሱልን ጠይቁልን” በማለት ሲገልጹ ይሰማል።