ህዳር 4 (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-40 በ60 እየተባለ የሚታወቀውና በቁጠባ ላይ የተመሰረተ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ከአዲስአበባ እና አካባቢ ምርጫ ጎን ለጎን ለማከናወን ኢህአዴግ ዕቅድ መያዙን ምንጮቻችን ጠቆሙ፡፡
በአቶ መኩሪያ ኃይሌ የሚመራው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስተባባሪነትና አመራር ሰጪነት በተለይ በአዲስ አበባ ለመጀመር የታቀደው ይህው ፕሮጀክት ከምርጫው ጎን ለጎን ለማስኬድ የተፈለገው ሕዝቡ ኢህአዴግ ለልማት የሚያደርገውን ጥረት ተረድቶ ልማቱን ለማስቀጠል ከጎኑ እንዲሰለፍ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡
በዚሁ መሰረት ለ40 በ60 ቤቶች የሚደረገው ምዝገባ በህዳር ወር መጨረሻ ተጀምሮ በቀጣይ ወራት እንዲካሄድ እንዲደረግ፣ በነዚህ ወራትም ለምርጫው የመራጮች ምዝገባ የሚከናወንበት ጊዜ በመሆኑ አጋጣሚውን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ለከፍተኛ ካድሬዎቹ መመሪያ ማስተላለፉን ምንጫችን ጠቁሟል፡፡
ምዝገባውንም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ለማከናወን ኃላፊነት የተሰጠው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ቢሮ መሆኑ ለቤት ምዝገባ የሚሰጡ መረጃዎች ገዥው ፓርቲ ዜጎችን ለመሰለል ተግባር ሊጠቀምበት ይችላል የሚለውን ሥጋት የሚያጠናክር ሆኗል፡፡
ቢሮው አምና ተመድቦለት ከነበረው 74 ሚሊየን በጀቱ ጋር ሲነጻጸር በ2005 በጀት ዓመት 128 ሚሊየን ብር በማደግ፤ ከፍተኛ በጀት ከተመደበላቸው መንግስታዊ ድርጅቶች አንዱ መሆን እንደቻለም ይታወሳል፡፡
ይህ መ/ቤት ከሕዝብ በተሰበሰበ ግብር ለሕዝብ አማራጭ ጥቅም የሚሰጡ መገናኛ ብዙሃንንና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን ለማፈን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
40 በ60 የሚባለው አዲስ ዕቅድ የቤቱን ጠቅላላ ወጪ 40 በመቶ ቤት ፈላጊዎች በአምስት ዓመታት ጊዜያት ከንግድ ባንክ ጋር በሚያደርጉት ስምምነት መሰረት ከቆጠቡ በኃላ ቀሪውን 60 በመቶ በብድር አግኝተው የቤት ባለቤት የሚሆኑበት አዲስ ፕሮግራም ነው፡፡
በተጨማሪም አነስተኛ አቅም ላላቸው ዜጎች ስቱዲዮ የሚባሉ ቤቶችን ለመገንባት ቤት ፈላጊዎቹ 10 በመቶ እንዲቆጥቡ ተደርጎ ቀሪው በባንክ በመሸፈን የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚረዳ ፕሮግራም ነው፡፡ሆኖም የመኖሪያ ቤት ፈላጊው ቁጥሩ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚገነቡ ጥቂት ቤቶችን በዕጣ የማከፋፈሉ ነገር እንደማይቀር ምንጫችን አስታውሶ ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ ብዙሃኑን የቤት ባለቤት ለማድረግ እንደማያስችል ገልጿል፡፡
ቀደም ሲል 20 በ 80 የሚባለው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ የ1997 ዓ.ም ምርጫ ታሳቢ አድርጎ ከ300ሺ በላይ ሕዝብ በመመዝገብ ቢጀመርም ከሰባት ዓመታት በኃላ የቤት ባለቤት መሆን የቻሉት ዜጎች ቁጥራቸው ከተመዘገቡት ከ1/3 ኛ በታች ናቸው፡፡ ይህ መረጃ ብቻውን ፕሮግራሙ በታሰበለት መልኩ ግቡን መምታት እንዳልቻለ የሚያሳይ ሲሆን አሁን ባለበት መልኩ ይቀጥል ቢባል ተመዝጋቢውን ብቻ ለማዳረስ ከ20 ዓመታት በላይ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚወስድ ተገምቷል፡፡