‹ ጋዜጠኛ እስክንድር የ 7 ዓመት ታዳጊ ህፃን ልጁን ናፍቆት እስክንድርን፦

ህዳር 4 (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ነገ ማክሰኞ ህዳር 4 ቀን 2005 ዓ.ም  በጋዜጠኛ  እስክንድር ነጋ ንብረት ዙሪያ ውሳኔ ለማሳለፍ  የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የሚሰየም ሲሆን፤ቃሊቲ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር   እዚያው እስር ቤት ትናንት የሁለት ቤት ካርታዎች የተያያዙበት መጥሪያ ደርሶታል።

 

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው ማስታወሻ ከሆነ፤ መንግስት ሊወስዳቸው ከተዘጋጁት ሁለት ቤቶች አንዱ በእናቱ ስም ያለ ሲሆን የዛሬ ዓመት አካባቢ ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል የቤቱን ስም ለማዞር ስትሞክር፦‹‹ካርታው የለም›› ተብላ ፤አንድ  ጊዜ ፦ ቀበሌ፣ ሌላ ጊዜ-ክፍለ ከተማ፣ ቀጥሎም- አዲስ አበባ መስተዳደር ስትመላለስ ከርማ ሊገኝ ስላልቻለ ሰልችቷት የተወችው ነው፡፡

 

ይሁንና ስንት ቦታ ሲፈለግ ያልተጘነው  የቤት ካርታ ትናንት ግን ከዓቃቢ ህግ የክስ ቻርጁ ጋር ተያይዞ  ቀርቧል።

 

<< ምንአልባት ያን ግዜ፦ ‹‹ካርታው የለም›› የተባለው ሆነ ተብሎ ተደብቆ ሊሆን ይችላል>>ብሏል-ጋዜጠኛ ተመስገን።
እስክንድር ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀርቦ፦ ‹‹ቤቴን አትውረሱብኝ›› ብሎ ስለማይከራከር ‹‹በዕለቱ ፍርድ ቤት መሄድ አልፈልግም›› ሲል ለማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፤ ማረሚያ ቤቱ ግን ‹‹የግድ ማቅረብ ስላለብን ይዘንህ እንሄዳለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡

 

እንደ ዘገባው ከሆነ፤  እስክንድር በዕለቱ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ምንም አይነት ምላሽ ላለመስጠት ወስኗል፡፡ ባለቤቱ ሠርካለምም  ፍርድ ቤቱ የፈለገውን ይወስን የሚል አቋም ስለያዘች፦ ‹‹የሚስትነቴን ድርሻ አትውረሱብኝ›› ብላ አትከራከርም፡፡
በመሆኑም  ጋዜጠኛ እስክንድር ትናንት ቅዳሜ ቃሊቲ እስር ቤት ሊጠይቀው ቃሊቲ የተገኘውን የሰባት ዓመቱን ህፃን ልጁን ጠባቂ ፖሊሶች እየሰሙት ድምፁን ከፍ አድርጎ፦ ‹‹ናፍቆት! እኔ ብሞትም አንተ ንብረቴን ታስመልሳለህ፡፡ አይዞህ! ስርዓት ተቀያየሪ ነው፤ ንጉሡ የወረሱት በደርግ ተመልሷል፤ ደርግ የወረሰው፤ በኢህአዴግ ጊዜ ተመልሷል፤ ኢህአዴግ የወረሰው ደግሞ ኢህአዴግ ሲወድቅ መመለሱ አይቀሬ ነው›› ብሎታል፡፡

 

በ1993 ዓ.ም ግምቱ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የእስክንድር እናት ቤት በግፍ እንደተወረሰ ይታወቃል፡፡