በጅጅጋ የሚታየው የሰብአዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

ህዳር ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፣ ሰራተኞችና ጎብኝዎች እንደገለጹት በኢትዮጵያ የሶማሊ ክልል ዋና ከተማ በሆነው ጅጅጋም ሆነ ከጅጅጋ ከተማ ራቅ ባሉ ቦታዎች ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተወላጅ የኦጋዴንና የሌሎችም ጎሳዎች አባላት እንዲሁም በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ የሌሎች አካባቢዎች ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ነው።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመንግስት ሰራተኛ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች በመሄድ በአካባቢው ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ሶማሊኛ አትችሉም ተብለው ከስራ ተባረዋል።

እንዲሁም በቀበሌ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ከ400 እስከ 1500 ብር የሚደርስ  ኪራይ እንዲከፍሉ በመገደዳቸው ምሬታቸውን እየገለጹ ነው።

የክልሉ መንግስት ልዩ ሚሊሺያ በማለት የሚጠራው፣  የፌደራሉ መንግስት ይወቀው አይወቀው የማይታወቅ፣  ታጣቂ ሀይል በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያለተቆጣጠሪ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸመ ነው።

ከመሀል አገር ወደ ጅጅጋ ለስራ የሄደ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ሰራተኛ  በአካባቢው የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ከተመለከተ በሁዋላ ለኢሳት እንደገለጸው ጅጅጋ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ አካል ናት ብሎ ለመናገር አያስደፍርም ብሎአል።

የክልሉ ልዩ ሚሊሻዎች በተወሰኑ ብሄር ተወላጆች ላይ አነጣጥረው ጥቃት እንደሚፈጽሙም ታዛቢው ይናገራል

ከአቶ መለስ ዜናዊ እረፍት በሁዋላ በክልሉ የሚታየው ግፍ እየጨመረ መምጣቱን ታዛቢው ገልጿል

ልዩ ሀይል እየተባለ የሚጠራው ታጣቂ ሀይል ከክልሉ አልፎ በአፋር ተወላጆች ላይ እስከ ሞት የሚደርስ ጥቃቶችን እየፈጸሙ እንደነበር በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አብዲ ሙሀመድ ኦማር፣ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ከእንግዲህ  ከማንም ትእዛዝ አልቀበልም በማለት ክልሉን ራዝ ገዝ አደርጋለሁ እያሉ ሲናገሩ እንደነበር የቅርብ ታማኝ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የክልሉን መንግስት አቋም ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።