ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ብቸኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፤ መንግስት ከመድረክ ጋር እንዲወያይ ጥሪ አቀረቡ።
በኢትዮጲያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ፤ መድረክ ከመንግስት ጋር በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት ይችል ዘንድ ጥሪ አቀረቡ።
የመድረክ ብቸኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፤ መንግስት ከታጣቂ ሃይሎች ጋር ለመወያየት ፈቃደኛነቱን እያሳየ፤ ከሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመወያየት ቀናኢነቱን አለማሳየቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
አቶ ግርማ ሰይፉ ከመንግስት ጋር ውይይት ለማድረግ ጥሪ ያቀረቡት ትላንት የሃገሪቱ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳልኝ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተገኝተው ከፓርላማ አባላት በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት መድረክ ነው።
የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ለኦጋዴን ነጻነት የሚታገል ታጣቂ ሃይል ሲሆን፤ በርካታ ጊዜያት ከመንግስት ሃይሎች ጋር ተዋግቷል። መንግስት ከዚህ ሃይል ጋር ከመስከረም ወር ጀምሮ በኬንያ በመደራደር ላይ ይገኛል። በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋርም መንግስት የመወያየት ፈቃደኝነት ሊያሳይ ይገባል ተብሏል።
መድረክ ለስልጣን የተለየ ናፍቆት የለውም ያሉት አቶ ግርማ ሰይፉ ይሁንና ከመንግስት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ በፖለቲካ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ ልንወያይ እንፈልጋለን ብለዋል።
ይሁንና፤ አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ፤ ለአቶ ግርማ ጥያቄ፤ በ2010 ዓ ም በተጠራው የፓርቲዎች ውይይት መድረክ ከገዢው ፓርቲ በተናጥል ካልሆነ አልወያይም ብሎ ወጥቷል፤ በማለት ለቀረበላቸው የእንወያይ ጥያቄ እንቢታን መርጠዋል።
አቶ ኃማሪያም ደሳልኝ አንዱን የፖለቲካ ፓርቲ በተናጥል በማወያየት ዴሞክራሲን መመስረት አንችልም ሲሉም መልስ ሰጥተዋል።
547 መቀመጫ ባለው የኢትዮጲያ ፓርላማ የተቃዋሚ ፓርቲ ያለው መቀመጫ በአቶ ግርማ ሰይፉ የተያዘው አንድ መቀመጫ ብቻ ሲሆን፤ ሁለተኛው ወንበር ኢህአዴግን በሚደግፉት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ተይዟል።