ከ200 ሺህ በላይ የኦሞ ሸለቆ ነዋሪዎች ለረሀብ ተጋልጠዋል

ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- “ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል” የተሰኘ ዓለማቀፍ ድርጅት በታችኛው የኦሞ ሸለቆ በመንግስት ከመሬታቸው የተፈናቀሉ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ለረሀብ ተጋልጠዋል አለ።

በታችኛው የኦሞ ሸለቆ በመንግስት አስገዳጅነት ከመሬታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች አርሰውም አድነውም ለመብላት ባለመቻላቸው በረሀብ ላይ መሆናቸው ተገለጠ::

በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ሞታቸውን እየተጠባበቁ ነው ተብሎል::

ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አለም ከረሀብ እና ከድህነት ጀርባ ያሉ ምክንያቶችን ለማሳወቅ በሚንቀሳቀስበት የዘንድሮው የአለም የምግብ ቀን፤ ኢትዮጵያ ግን የምግብ ዋስናን አደጋ ውስጥ በመጣል 200 ሺህ ዜጎቾን አፈናቅላ ለረሀብና ለእልቂት ዳርጋለች ብሏል::

መንግስት ታጣቂዎቹን አሰማርቶ በሀይል ከእርሻና ከግጦሽ መሬታቸው ያፈናቀላቸው የሙርሲ፣የሱሪ፣የቦዲና የኩዊጉ ጎሳ አባላት፤ ከብቶቻቸውን የሚያስግጡበት ለራሳቸውም የሚያርሱበት መሬት በማጣታቸው ከሞትና በህይወት ጋር ተፋጠው ይገኛሉ ብሏል የሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል መግለጫ::

ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ያናገረው አንድ የሱሪ ጎሳ አባል “መሬታችንን መንጥረውታል፣ ለምንስ መሬታችንን መንግስት ሸጠብን? ለከብቶቻችን ሳር የለንም! ሰዎቻችንም እየተራቡ ነው! ሁላችንም እየተራብን ነው! ተስፋም አጥተናል” ሲል ተናግሮል::

መንግስት ከአካባቢው ሰው ጋር ሳይወያይ ያካሄደው ማፈናቀል፤ የግልገል ጊቤን ቁጥር ሶስት ግድብ ለመገደብ እና ሰፋፊ የጥጥና የሸንኮራ ማሳ ለማስፋፋት በሚል ቢሆንም፤ ይህ እርምጃ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የአካባቢውን ህዝብን ለረሀብና ሞት የሚጋብዝ ነው ይላል ሪፖርቱ::