“ወደ ሥልጣን የመጣው አመራር ባለፈው መንገድ ሊቀጥል አይችልም” ሲሉ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አስጠነቀቁ

ጳጉሜን ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- “በቀጣይ በኢትዮጵያ የተሸለ ነገር የሚመጣው፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ተገናኝተው፣ በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ተመካክረው መፍትሔ ማምጣት የሚችሉበት ዕድል ሲፈጠር ብቻ ነው።” ሲሉ አቶ ቡልቻ ወደ ሥልጣን እየመጣ ላለው አዲስ አመራር ቡድን መልዕክት አስተላለፈዋል።

የቀድሞው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀ-መንበር ይህን ያሉት፤ዛሬ ለንባብ ከበቃው ሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።

“ከጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በኃላ አስተዳደሩን ከተረከበው አዲስ አመራር ምን ይጠበቃል?” በማለት ጋዜጣው ላቀረበላቸው የመጀመሪያ ጥያቄ አቶ ቡልቻ ፦” አዲስ አመራር አለን’ንዴ?”በማለት ነበር ጥያቄውን በጥያቄ  የመለሱት።

 

“በአሁኑ ሰዓት በግልጽ የሚታወቅ አዲስ አመራር የለም እያሉ ነውን?”በማለት ለቀረበላቸው ተከታይ ጥያቄም ፦”አዎ የለም! ሕዝቡ ደግሞ መሪው ማን እንደሆነ  የማወቅ መብት አለው።”ብለዋል-  የቀድሞው የኦፌዲን ሊቀ-መንበር።
“ መጀመሪያ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአሁኑ ጊዜ አገሪትዋ ምን ዓይነት አመራር ያስፈልጋታል? ብሎ መጠየቅ አለበት። እኔም እጠይቃለሁ። “ ያሉት አቶ ቡልቻ፤እስካሁን ድረስ አንድ ፓርቲ፣ ያውም ዝግት ያለ ፓርቲ… ሌላ ኀሳብና አማራጭ የማይቀበል እና የማያስተናግድ ፓርቲ ላለፉት 21 ዓመታት ሲመራን ቆይቷል” ብለዋል።

አያይዘውም፦”አመራሩ ከዛሬ 21 ዓመታት በፊት ይዞት የመጣውን የራሱን ኀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ይሞክራል። ኀሳብ አይለወጥም’ንዴ? ታላቁ የአሜሪካ መንግስት እንኳን በየአራት ዓመቱ አመራሩን ይለውጣል። ፖሊሲ ባይለውጥ እንኳን አመራሩ መለወጡ ጥሩ ነገር ነው። 21 ዓመታት ሙሉ በአንድ አመራር ብቻ፣ በአንድ ፍልስፍና ብቻ፣ በትግል ላይ ተገናኘን በሚሉ ጥቂት ሰዎች ብቻ ኢትዮጵያን ያህል አገር እንዴት ትመራለች? “ ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀዋል።

በቀጣይ በኢትዮጵያ የተሸለ ነገር የሚመጣው የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ተገናኝተውና በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ተመካክረው መፍትሔ ማምጣት የሚችሉበት ዕድል ሲፈጠር ብቻ ነው ሲሉም አቶ ቡልቻ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

“የአቶ መለስ ህልፈተ ሕይወት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ነገር እንዲፈጠር ያደርጋል ብለው ያምናሉ?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ቡልቻ ፤“ አዎ…ትልቅ ለውጥ መምጣት አለበት”ብለዋል።-ኢህአዴግ እና አቶ መለስ አገሪቷን የመሩበት አቅጣጫ ፤ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ያረካና  ያስደሰተ እንዳልነበረ በማስረገጥ።

ይህ ሁሉ በአቶ መለስ ቀብር ላይ የተገኙ የውጪ አገር ሰዎች ባደረጉት  ንግግርና በሰጡት ምስክርነት የኢትዮጵያ ሕዝብ፦” ጥያቄዬ መልስ አግኝቷል ብሎ ቤቱ አርፎ የሚቀመጥ ይመስልሃልን?”ሲሉም አቶ ቡልቻ ጠይቀዋል።

እንደ ቀድሞው ኦፌዲን ሊቀመንበር  ገለፃ፦የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ትልቅ ለውጥ እየጠበቀ ነው ።

ሰሞኑን ሐዘኑን ለመግለጽ የወጣው ሕዝብ ለኢህአዴግ እግረመንገድ ድጋፉን ሰጥቷል እየተባለ ነው  የተባሉት አቶ ቡልቻ፤አቶ መለስ እንደማናቸውም ሰዎች ዘመዶች ፣ የሚወዷቸውምና የሚደግፏቸውም ሰዎች እንዳሏቸውና ከዚህ አንጻር ለሐዘን ሰው መውጣቱ የሚያስገርም እንዳልሆነ፤ እንዲሁም ለሞተ ሰው ማዘን ፤ለፓርቲ ያለ ድጋፍን  እንደማያመለክት አስረድተዋል።

አቶ ቡልቻ አክለውም፦” ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወጥቶ አላለቀሰም። ለምን ብትል ብዙ ቁስል ያለበት ህዝብ አለ። የዛሬ አራት ዓመት በአንድ ቀን ከቀትር በኋላ ብቻ በኦሮሚያ 200 ሰዎች የተገደሉበት ሁኔታ እንዴት ይረሳል? በ1997 ዓ.ም የወለጋ ሕዝብ ጦርነት ተከፈተበት፤ መዓት ሰዎች አለቁ፤ ማሳቸው ተቃጠለ፤ የተቀሩት ተሰደዱ፤ ይህ ይረሳስ ቢባል እንዴት ይረሳል? ለአቶ መለስ የሚያለቅስላቸው ቢኖርም ፤እጅግ የበዛው ያላለቀሰላቸውና ያዘነባቸው ሕዝብ ነው። ባለፉት ዓመታት በዚህ ሥርዓት ብዙ ሰዎች ታስረዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተንገላተዋል፣ ተሰደዋል። ብዙ ቤተሰቦች ተበትነዋል። ይህንን እውነታ ማንም ሊክደው አይችልም። ሰዎች ለአቶ መለስ ስላለቀሱና ስላዘኑ ብቻ ለኢህአዴግ ድጋፍ ሰጡ ማለት የማይቻለው ከዚህ አንጻር ነው። ለነገሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ለአቶ መለስ ቢያለቅስ እንኳን ፤ለኢህአዴግ ድጋፍ ሰጠ ማለት አይቻልም።”ብለዋል።

አዲሱ አመራር በአቶ መለስ ጅምር መንገድ እቀጥላለሁ ማለቱም ፈፅሞ የሚያዋጣ እንዳልሆነ ነው አቶ ቡልቻ የተናገሩት።
“ በሕግና በፖለቲካ ተደግፎ በሕዝብ ላይ ትልቅ ግፍ ሲሰራ የነበረው ኢህአዴግ በዚህ መንገድ ሊቀጥል ነውን?“ በማለት የጠየቁት አቶ ቡልቻ፤ “ይህን ዓይነት አካሄድማ ማንም ኢትዮጵያዊ አይደግፈውም።  ስንትና ስንት ጉድፎችን ተሸክሜ በቀድሞው አገዛዝ እቀጥላለሁ ማለት፤ ሕዝብን ተስፋ ማስቆረጥ ነው።” ሲሉ አስገንዝበዋል።

 

አቶ ቡልቻ ከሁለት ቀናት በፊት ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ለአቶ መለስ ሞት የተካሄደውን  የተንዛዛ የለቅሶ ሥርዓትና በቀብራቸው ላይ በውጪ መንግስታት ተወካዮች ስለ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተሰጠውን የተጋነነ ምስክርነት አጠንክረው መተቸታቸው ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide