ጥር 9 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ( ኢሰመጉ) የሚለውን ስያሜውን በመንግስት ጫና ወደ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ለመለወጥ የተገደደው ብቸኛው የኢትዮጵያ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ተቋም ሰሞኑን ባወጣቸው ሁለት ልዩ መግለጫዎች፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ መሆኑን አጋልጧል ።
ሰመጉ በ118ኛ እና በ119ኛ ልዩ መግለጫው የተፈፀሙትን የመብት ጥሰቶች በስፋት በመዘርዘርም፤ የእርምት እርምጃ እንዲወስድባቸው ለሚመለከታቸው መንግስታዊና ዓለም አቀፍ አካላት አቤት ብሏል።
ሰመጉ በ118ኛ ልዩ መግለጫው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል ያለው በደቡብ ክልል፣ በከፋ ዞን፣ በገዋታ ወረዳና ዙሪያ ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ የሚኖሩ ቁጥራቸውም 50ሺህ የሚገመቱ የኦሮሞ ተወላጆች ፤ልጆቻቸው በራሳቸው ቋንቋ የመማር ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና በማኅበር ተደራጅተው በልማት ለመንቀሳቀስ በመጠየቃቸው፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል ብሏል።
ነዋሪዎቹ፤ በሕገ-መንግስቱ የተሰጣቸው መብት እንዲከበር ጥያቄ በማቅረባቸው ምክንያት፤ ለሕገ-ወጥ እስራት፣ ማስፈራራት፣ የቤት እና ንብረት ቃጠሎ፣ ለሕገ-ወጥ የመኖሪያ ቤት ብርበራ፣ በቀበሌ አመራር ላይ እንዳይሳተፉ የመከልከል እና ሌሎችም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደደረሱባቸው ሰመጉ አመልክቷል።
እነዚሁ የ ኦሮሞ ተወላጆች ጥያቄአቸውን ከወረዳ እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰላማዊ መንገድ አቅርበው መብታቸውን ለማስከበር በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት ብዙ በደል እንደደረሰባቸው የጠቀሰው መግለጫው፤ በዶማ ቀበሌ ጳጉሜ 2 ቀን 2003 ዓ.ም የ10 ቀበሌ ሕዝብን በመጥራት ስብሰባ በተደረገበት ወቅት፤ የወረዳው ባለስልጣናት በገዋታ ወረዳ የሚኖሩ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች፦ “ልክ ስላልሆነ አይፈቀድላቸውም፤ በእኛ ስር ዝቅ ብላችሁ መኖር አለባችሁ። ለዚህ ፈቃደኛ ካልሆናች፤ አሸባሪዎች ናችሁ” መባላቸውንም አትቷል።
ጥያቄ ካቀረቡት የ ኦሮሞ ተወላጆች መካከል ዕድሜአቸው ከ32 እስከ 62 የሚደርሱ 20 ሰዎች መታሰራቸውን እንዲሁም 32 የሚሆኑ ሰዎች ንብረታቸው እንደተቃጠለባቸውና ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ በስም፣ በጾታ እና በዕድሜ በመለየት መግለጫው ዘርዝሯል።
በሌላ በኩል በዚሁ በደቡብ ክልል፤ በጋሞ ጎፋ ዞን፤ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በብላንቴ ቀበሌ ውስጥ የደን መውደምና ሕገ-ወጥ የመሬት ክፍፍል በመደረጉ፤ ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ለሚመለከታቸው ክፍሎች አቤቱታ ሲያሰሙ መቆየታቸውን ሰመጉ በ119ኛ ልዩ መግለጫው ላይ ጠቅሷል።
በላንቴ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር 960 አባወራዎችና 6000 የሚገመት ሕዝብ እንደሚኖር ያመለከተው መግለጫው፤ ስፋቱ 20 ጋሻ መሬት ላይ 60 ሔክታር የተፈጥሮ ፣ 15 ሔክታር የሚሊኒየም ፓርክ እና በባሰ ተፋሰስ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ የተከለው 30 ሔክታር የሚገመት ባህርዛፍና ሌሎች ዛፎች እንደሚገኙ ያወሳል።
ሆኖም የላንቴ ቀበሌ የመሬት ዴስክ ኃላፊና የቀበሌው ሊቀመንበር፤ ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የካቢኔ አባላት፤ እንዲሁም ከዞንና ከክልል ሀላፊዎች ጋር በመመሳጠር በርካታ ባለስልጣናት በሕገ-ወጥ መንገድ መሬት ለራሳቸው፣ ለዘመዶቻቸው፣ መሬት ላላቸው ገበሬዎች፣ ለፖሊሶች፣ ለመንግስት ሰራተኞችና ከሌላ ቀበሌ ለመጡ ሰዎች ያለመመሪያና ደንብ መደልደላቸውን የጠቀሰው መግለጫው፤ይህን የተቃወሙ 33 ሰዎች ከመስከረም 30 ቀን 2004 እስከ ጥቅምት 16 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ በሕገ-ወጥ መንገድ መታሰራቸውን ገልጿል ።
እስሩም በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 17(1) እና የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ድንጋጌዎች አንቀፅ 9 ላይ፦” ማንኛውም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ አይችልም” የሚለውን ድንጋጌ የጣሰ መሆኑን ሰመጉ አመልክቷል።
ከታሰሩት 33 ሰዎች በተጨማሪ ሦስት ሰዎች ቤያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መታሰራቸውንና ቤታቸው መፈተሹን ፤ይህንንም ድርጊት ያጋለጡ ሁለት የልማት ሰራተኞች እንዲታሰሩና ከስራቸውም እንዲታገዱ መደረጉን ሰመጉ ጠቁሟል።
በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ጋሴሬና ካራቻ ቀበሌ በሚኖሩ በ19 አባወራዎችና በ200 ቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ ተመሳሳይ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን ሰመጉ አጋልጣል።
እነዚህ ነዋሪዎች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በይዞታ መሬታቸው ላይ የተለያዩ ዛፎችንና አትክልቶችን አልምተው የሚኖሩ ሲሆን፤ ያለምንም ካሳ መሬታቸውን ለአንድ ባለሃብት ተሰጥቶባቸዋል ብሏል።
ባለሀብቱ ቦታውን ከነዋሪዎቹ የመቃብር ስፍራ ጋር በመጨመር አንድ ላይ በማጠራቸውም፤ አንድ የአርሶ አደር ከብት ወደታጠረው ቦታ ከገባ እስከ መቶ ብር እንዲከፍል ይደረጋል እንደ ሰመጉ መግለጫ ።