የኢትዮጵያ ህዝብ ማንንም ሳይጠብቅ ለነፃነቱ እንዲነሳ ጄኔራል ከማል ገልቹ ጥሪ አቀረቡ

ጥር 9 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-ህብር ራዲዮ ከላስቬጋስ እንደዘገበው፤የመገንጠል ሀሳቡን ከፕሮግራሙ ያወጣው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር ጄኔራል ከማል ገልቹ፤ በአሁኑ ወቅት የግንባሩ ዋነኛ ዓላማ በተባበረ የኢትዮጵያ ህዝብ ክንድ ወያኔን በማንበርከክ ለህዝቡ ጥያቄ እንዲገዛ ማድረግ መሆኑን በድጋሚ በማረጋገጥ፤ ህዝቡ ሳይከፋፈልና ማንንም ሳይጠብቅ ለነፃነቱ እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ህብር ዘገባ፤ጄኔራል ከማል  ይህን ጥሪ ያቀረቡት፤እሳቸው የሚመሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፤ በቅርቡ የመገንጠል ፕሮግራሙን  በመተውና የኢትዮጵያ ህልውናን በመቀበል ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ተባብሮ ለመታገል መነሳቱን አስመልክቶ  ለተሰነዘሩባቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።

 ጀነራል ከማል በዚሁ ምላሻቸው፤ የነፃነት ትግሉን ወደፊት ለመግፋት ያስችላል ያሉትን የኦነግ ዓላማን አብራርተዋል። ኦነግ ፤ለትግል እንቅፋት ይሆናሉ ያላቸውን ነገሮች ማስተካከሉን የገለፁት ጄኔራል ከሚል ህዝቡ ይህን መንገድ ተከትሎ ማንንም ሳይጠብቅ ራሱን ነፃ እንዲያወጣም  በአጽንኦት አሣስበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ በስልጣን ላይ ያለውን የግፍ ስርዓት እንዲያስወግድ ከተፈለገ ፤የተቃውሞ ትግሉን የሚመሩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ወገኖች መተባበር እንዳለባቸውም  ጀነራሉ ሳይጠቁሙ አላለፉም።

“ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝብ ክንድ ከተንበረከከ በሁዋላስ- ምን አይነት መንግስት ይመሰረታል?” በሚለው አብይ ጥያቄ ዙሪያ የድርጅታቸውን አቋም ሲገልጹም፦” ኦነግ ከሌሎች ጋር በመሆን ምን አይነት አገር መመስረት እንዳለበት እንደሚነጋገርና ግንባሩም ለህዝቡ የሚያቀርበውን አማራጭ እንደሌሎቹ ድርጅቶች ሁሉ ለህዝቡ አቅርቦ በህዝቡ ውሳኔ የወደፊት እጣውን እንደሚወሰን አመልክተዋል ።

ጄኔራል ከማል ገልቹ፤ የአቶ መለስ አስተዳደርን አውግዘው ከመከላከያ ሰራዊቱ የተለዩት ምርጫ 97ን ተከትሎ ወያነ ሰራዊቱን ሽፋን በማድረግ በህዝቡ ላይ  የወሰደውን ህገ-ወጥ ግድያ በመቃወም  ቢሆንም፤  እ.ኤ.አ ከ2001 ጀምሮ በህቡዕ በኦነግ  አመራር ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸው ገልፀዋል።