40 ሚሊዮን ብር የወጣበት የጣናን ደለል ለመጥረግ የተገዛው ማሽን ያለ ስራ በዝገት ሲበላ ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም ተባለ

40 ሚሊዮን ብር የወጣበት የጣናን ደለል ለመጥረግ የተገዛው ማሽን ያለ ስራ በዝገት ሲበላ ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም ተባለ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 09 ቀን 2010 ዓ/ም) ኢሳት ትናንት ሰኞ አንድ የመንግስት ባለስልጣንን ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የጣና ደለልን ለመጥረግ የተገዛው ማሽን ያለ ስራ መቀመጡን ገልጾ ነበር። ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች ለኢሳት እንደገለጹት ባለስልጣኑ የሰጡት መረጃ የተዛባ ነው።
ማሽኑ የተገዛው በውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስቴር በጣና በለስ የተቀናጀ የውሀ ሀብት አስተዳደር ሲሆን ይህ ፕሮጀክት የሚንቀሳቀሰው በአለም ባንክ ብድር እና ከፊንላንድ መንግስት በተገኘ እርዳታ ነው፡፡ ይህ የደለል መጥረጊያ “ ድሬጅግ ማሽን” ጣና ውስጥ ያለውን ደለል እስከ 500 ሜ/ር በተገጠመለት ሁዝ አውጥቶ የሚጥል ሲሆን፣ ማሽኑ በ2007 ዓ.ም ከጣሊያን ድርጅት በ 1.3 ሚሊዮን ዩ ወይም በአሁን ምንዛሬ ከ33 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ወጥቶበት ወደ አገር ውስጥ የገባ ነው፡፡
የጣሊያኑ ድርጅት ሁዝ የተባለውንና ሌሎች እቃዎችን አብሮ ባለማቅረቡ ማሽኑ ስራ አለመጀመሩንም የሚገልጹት ምንጮች፣ ሚንስቴሩም እቃዎች ካልመጡ ቀሪ ክፍያውን አልከፍልም ካለ በሁዋላ፣ ችግሩ የተፈጠረው በሚንስቴሩ ነው በመባሉ በጣሊያን ኢምባሲ ግፊት ገንዘቡ ግዢ ለተፈጸመበት ኩባንያ እንዲከፈል ተደረጓል፡፡
ለፕሮጀክቱ ድጋፍ የሚያደርጉት የአለም ባንክ ባለሙያዎች ችግሩን በማየት ከእንዶኒዠያ አማካሪ ባለሙያ በማስመጣት እንዲመረመር ያደረጉ ሲሆን፣ ማሽኑ ሲፈተሽ ተጨማሪ 7 ሚሊየን ብር የሚያወጣ እቃ እንደሚያስፈልግ ተገልጾ የእቃዎ ግዥ ተፈጽሟል፡፡
ማሽኑ በአጠቃላይ 40 ሚሊየን ብር ገደማ አስወጥቶ ከተገዛበት ከ2007 ዓም ጀምሮ እስካሁን ድረስ አገልግሎት ሳይሰጥ የቆመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከነበረው ችግር በተጨማሪ በዝገት በመበላት ላይ መሆኑ ሌላ ችግር መፈጠሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ማሽኑን በሃላፊነት የሚረከበው ባለቤት መጥፋቱም ታውቋል። የአባይ ተፋሰስ ለጣና ትራንሰፖርት ድርጅት አስረከቤአለሁ በማለት በማለት የማይሰራ ማሽን ጭኖ ጎርጎራ ወስዶ ማስቀመጡን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።