ወ/ሮ አና ጎሜዝ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንደሚቆም ገለጹ

ኢሳት ዜና (ጥር 12 ፥ 2008)

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በኢትዮጵያ መንግስትና በጸጥታ ሃይሎቹ በህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በፅኑ ማውገዙን ተከትሎ የአውሮፓ  ህብረት ፓርላማ አባል ወ/ሮ አና ጎሜዝ የአውሮፓ ህብረት ምንጊዜም ከኢትዮጵያውያን ጎን እንደሚቆም ገለጹ።

የህብረቱ ፓርላማ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ ጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ 140 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ እንዲያይ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን  አመጽና ከግንቦት 2007 የፓርላማና የክልል ምርጫ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ እና እየተፈጸሙ ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲመረምር ግልጽ፣ ቀጥተኛና፣ ገልተኛ አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም በአጽንዖት ጠይቋል።

ኢሳት የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል የሆኑትን አና ጎሜሽን ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን አናግሯቸው ነበር። ወ/ሮ አና ጎሜዝ “የውሳኔ ሃሳቡ በሰባት ሃይል ባላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ያለምንም ተቃውሞና ማሻሻያ ተቀባይነት ያገኘ ነው። ፓርላማው በኢትዮጵያ ላይ ባለፉት 10 አመታት በሰብዓዊ መብት፣ በዲሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ካሳለፋቸው ጠንካራ ውሳኔዎች የመጀመሪያው ነው” ብለዋል።

ወ/ሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሌላውም የኢትዮጵያ ክፍል ማለትም ኦጋዴን፣ ጋምቤላ፣ እና በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በጋዜጠኞች፣ በፖለቲካ ፓርቲ አባላትና በህዝቡ በሲቢክና በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እየተፈጸመ እንደሆነ የአውሮፓ ህብረት ተገንዝቧል፥ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ በዚህ መቀጠል አይችልም የሚል አቋም ይዟል” ሲሉ አክለው አስረድተዋል።

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በመግለጫው እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የመረጃ ፍሰትን አፈና እንዲያቆሙ፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እንዲያጎናጽፉና ነጻ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በአገሪቷ በሙሉ ነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲፈቅድ ጥሪ አቅርቧል።

የአውሮፓ ህብረት እንደብቸኛ ግዙፍ አርዳታ ሰጪ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው እርዳታ ለሰብዓዊ መብት አፈና መዋል እንደሌለበት ማረጋገጥ እንደሚኖርበት አሳስቧል።

የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል አና ጎሜዝ ለኢሳት እንደተናገሩት የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ የቀረበውን ሃሳብ ያለምንም ማሻሻያ ሙሉ በሙሉ ጸድቋል።

ወይዘሮ አና ጎሜዝ ለኢሳት እንደተናገሩት በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስት ትዕዛዝ በጸጥታ ሃይሎች በሚደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እጅግ በጣም ማዘናቸውን ገልጸዋል።

“ከኢትዮጵያ ህዝብ አብረን እንቆማለን፥ እያሽቆለቆለ በመጣው የሰብዓዊ መብት አያያዝ አሳስቦናል” በማለት  ወይዘሮ አና ጎሜዝ ለኢሳት በስልክ ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን በመሬት ወረራ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በመሳሰሉት ሂደቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታ እየተበላሸ ሊሄድ እንደሚችል ወይዘሮ አና ጎሜዝ ገምተዋል።