የብሪታንያ መንግስት እንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ ጥሪ እንዲያቀርብ ሪፕሪቭ የተሰኘ ተቋም ጠየቀ

ኢሳት (ጥር 12 ፥ 2008)

የብሪታኒያ መንግስት ከቀናት በኋላ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት ልዩ የመሪዎች ጉባዔን በመጠቀም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ ጥሪዎን እንዲያቀርብ ሪፕሪቭ የተሰኘ የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተቋም ሃሙስ አሳሰበ።

በዚሁ ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የብሪታኒያውን የውጭ ጉዳይ ቢሮ ሚኒስትር የሆኑት ጀምስ ዱድሪጅ ወደ አዲስ አበበ ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሃላፊው ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ ተከትሎም የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተቋም ለጀምስ ዱድሪጅ የጹሁፍ መልዕክትን ያቀረበ ሲሆን በመልዕክቱም ሚኒስቱ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ እንዲያደርጉት ጠይቋል።

“ወደ አዲስ አበባው የአፍሪካ ልዩ የመሪዎች ጉባዔ የሚወከሉት የብሪታኒያ ባለስልጣናት ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈታ ብርቱ ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል” ሲሉ የተቋሙ የሞት ቅጣትን የሚከታተለው ክፍል ሃላፊ ማያ ፎአ አስታውቀዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ የጤናቸው ሁኔታ እጅግ እያሽቆለቆለ መምጣቱ አሳስቦት እንደሚገኝም የብሪታኒያው የሰብዓዊ መብት ድርጅት ባወጣው መገለጫ አመልክቷል።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የአእምሮ ጤንነት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ በሌሎች አካላት ጭምር መረጋገጡና በመግለፅ ላይ መሆኑንም ሪፕሪቭ ተቋም አክሎ አስታውቋል።

ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ የሚጀመረው የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳውን በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚካሄድ ሲሆን የብሪታኒያ መንግስት ይህንኑ አጀንዳ በመጠቀም ለኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥያቄው እንድያቀርብ ድርጅቱ ጠይቋል።

በርካታ አለም አቀፍ ድርጅቶች የብሪታኒያ መንግስት አንዳርጋቸው ለማስፈታት የተለሳለሰ አቋምን ይዟል ሲሉ ተቃውሞ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።