በኢትዮጵያ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ወደከፋ የረሃብ ቀውስ ሊቀየር እንደሚችል ተገለጸ

ኢሳት (ጥር 12 ፥2008)

በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ የሚገኘው የድርቅ አደጋ በተያዘው የፈረንጆች አዲስ አመት ወደከፋ የረሃብ ሰብዓዊ ቀውስ ሊለወጥ እንደሚችል ካሪታስ ኢንተርናሽናል የተሰኘ የሰብዓዊ እርዳታ ተቋም ሃሙስ አሳሰበ።

በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ጉዳትን እያደረሰ የሚገኘው ይኸው የድርቅ አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ አለም አቀፍ ርብርብ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ መድረሱንም ድርጅቱ ገልጿል።

በሃገሪቱ ያለው የድርቅ አደጋ አስከፊ ገጽታን ከመያዙ በፊት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ዛሬውኑ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል ሲሉ የካሪታስ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሃፊ ሚቼል ሮይ ለባቲካን ራዲዮ አስታውቀዋል።

በአለም አየር ለውጥ ሳቢያ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጭምር ቢስተዋልም ጉዳቱ በኢትዮጵያ የተለያየ ገጽታ አለው ሲሉ ሃላፊዋ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥ የከፋ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው ከፍተኛ የውሃ እጥረትና የእርዳታ እህል አቅርቦት መዘግየት ችግሩን ኣያባባሰው እንደሚገኝ እነዚሁ አካላት ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ወቅታዊ ምላሽን ባለማድረጉ ሳቢያ የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በመግለጽ ድርቁ ወደከፋ ደረጃ እንዳይደርስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በድጋሚ አስታውቀዋል።

ይሁንና አለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በሃገሪቱ የመጠባበቂያ የምግብ ክምችት እየተመናመነ መምጣቱንና የምግብ ዋጋ በማሻቀብ ላይ መሆኑን ችግሩን እያወሳሰበው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከቀናት በፊትም የህጻናት አድን ድርጅቶች ጥምረት በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በህጻናት ላይ ኣያደረሰ ያለው ጉዳት ጦርነት በሶሪያ ህጻናት ላይ ከሚያደርሰው ሰብዓዊ ቀውስ ጋር ተመሳሳይ እያሆነ መምጣቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በተያዘው አመት በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ በሃገሪቱ ታሪክ በ 50 አመት ውስጥ ሲከሰት የከፋው እንደሆነ ተነግሯል።