የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ግድያ አወገዘ

ኢሳት (ጥር 12 ፥ 2008)

በወቅታዊ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የመከረው የአውሮፓ ፓርላማ ባሰራጨው መግለጫ በኢትዮጵያ የመንግስት ሃይሎች በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ግድያ አውግዟል።

በዚሁ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ባለው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ከተገደሉ ሰዎች በተጨማሪ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የአውሮፓ ፓርላማ ገልጿል።

በተለያዩ አለም አቅፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በኢትዮጵያ የፓርቲ አካላት ይፋ የተደረገው የ 140 በላይ ሰዎች ግድያም በአስቸኳይ በገልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ፓርላማው አስነብቧል።

ባለፈው አመት ግንቦት ወር የተካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎም በሃገሪቱ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና እስራቶች ተመሳሳይ የማጣራት እርምጃ እንዲካሄድባቸው የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ጠይቋል።

ገዢው የኢህአዴግ መንግስት መቶ በመቶ ለድል ያበቃበትን ይህንኑ ምርጫ ምክንያት በማድረግ በርካታ ሰዎች ጋዜጠኞችና የፓርቲ አመራሮች አባላት ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ሃሳባቸውን በነጻነት በሚገልፅ አካላት ላይ የሚወሰደውን የሃይል እርምጃና አፈና በማቋቋም የዜጎች የመናገር መብትን እንዲያከብር የፓርላማ ቡድኑ በጽኑ አሳስቧል።

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍም የሰብዓዊ መብቶችን ለመጣስ በሚደረጉ ተግባራት ላይ እንዳይውሉ ማረጋገጥ ይኖርበታል ሲል የአውሮፓ ህብረት አክሎ ጠይቋል።

የፓርላማ ቡድኑ ሃሙስ ያስተላለፈውን የውሳኔ ሃሳቦች ተከትሎም የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር የሆነው የአውሮፓ ህብረት የአቋም ማስተካከያዎችን ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአውሮፓ ህብረትና ከሌሎች አጋር አገራት በየአአመቱ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍን የሚያገኝ ሲሆን፣ ይህም በአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ ይነገራል።

ህብረቱ በሀገሪቱ ላይ የሚይዘው አቋምም በኢትዮጵያ የፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ኣንደሚያስከትል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች በመግለጽ ላይ ናቸው።