በኢትዮጵያ የሚሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥር ጨምሯል

ነሃሴ ፳፮(ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የጸረ ሽብር አዋጁን ተገን በማድረግ በጋዜጠኞች ላይ የተከፈተውን ዘመቻ ተከትሎ፣ አገር ጥለው

የሚወጡ የነጻው ፕሬስ አባላት ቁጥር መጨመሩን መረጃዎች አመልክተዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ12 ያላነሱ ጋዜጠኞች ከደህንነት ሃይሎች በደረሰባቸው ጫና ምክንያት አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ሲሆን፣ ብዙዎቹ በስደት

በሚኖሩባቸው አገሮች ለችግር ተዳርገዋል። የኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ያለ ተቆጣጣሪ ገብተው በሚወጡባት ኬንያ የሚገኙ ጋዜጠኞች በስጋት ውስጥ

መሆናቸውን ኢሳት ያነጋገራቸው ጋዜጠኞች ገልጸዋል።

ባለፉት 2 ቀናት የተሰደደውን፣  በተለያዩ መጽሄቶች ላይ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች በመጻፍ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ብስራት

ወ/ሚካኤልን ጨምሮ ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ፣ ተሰማ ደሳለኝ፣ ዘሪሁን ሙሉጌታ፣ መላኩ አማረ፣ ግዛው ታየ፣ ቶማስ አያሌው፣ ሰብለወርቅ መከተ፣

አቦነሽ አበራ፣ ሰናይ አባተ፣ አስናቀ ልባዊ፣ ሲሳይ ሳይሌ፣ እንዳልካቸው ተስፋየ፣ ኢብራሂም ሻፊ፣ እንዳለ ተሺ፣ ሀብታሙ ስዩም፣ ዳዊት ሰሎሞንና

ዳንኤል ድርሻ የተባሉ ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች ተሰደዋል። ጋዜጠኛ በትረ ያእቆብ፣ ብስራት ወ/ሚካኤልና ዘሪሁን ተስፋየ በቅርቡ የተቋቋመው

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ህብረት ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በመሆን ሰርተዋል።

የተሰደዱት ጋዜጠኞች ኢቦኒ፣ ሰንደቅ፣ ሊያ፣ ሎሚ፣ አፍሮ ታይምስ፣ ጃኖ፣ ፒያሳና አዲስ ጉዳይ በተሰኙት መጽሄቶች  ላይ ሰርተዋል።

መንግስት በጋዜጦች ላይ የሚወስደው እርምጃ ከመጪውን ምርጫ ጋር የተያያዘ ነው በሚል ይተቻል። ዞን ዘጠኝ እየተባሉ የሚጠሩ በማህበራዊ ድረገጾች

ላይ የሚሳተፉ ጸሃፊዎች  እንዲሁም በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራቸው ሃብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ የሽዋስ አሰፋና ዳንኤል

ሽበሺ መታሰራቸው ገዢው ፓርቲ መጪውን ምርጫ ያለምንም ችግር ለመለፍ የወሰደው እርምጃ ነው በማለት የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጻቸው ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያን ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት ጥሰትና ዲሞክራሲ ሁኔታ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አለመስማማታቸውን

ሪፖርተር ዘግቧል።

ጋዜጣው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የህብረቱ አባላት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት

ባለስልጣናት በተገኙበት በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና ተያያዥ ጉዳዮች ውይይት ሲያደርጉ በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ

ቀርተዋል።

መንግስት ከአውሮፓ ህብረት የቀረበውን ትችት ሳይቀበለው መቅረቱንም ባለስልጣኑ ገልጸዋል።