ሰኔ ፬(አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በቡራዩ ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ መርተዋል የተባሉ 7 ወጣቶች ሰኔ 3 ቀን 2006 ዓም ፍርድ ቤት በቀረበቡበት ወቅት 5 ፖሊሶች እና አንድ የኢህአዴግ ባለስልጣን በእስረኞች ላይ ለመመስከር መቅረባቸው ታውቋል።
በመዝገብ ቁጥር 48 ሺ 385 የተከሰሱት ፈይሳ አብዲሳ ገለታ፣ ፋይሳ ጉታ ረጋሳ፣ ታደላ ቶሎሳ ቱሉ፣ ሽሮምሳ ፋይሳ፣ ጆቲ ተመስገን፣ ከተማ ባሼ እና ስራታ ለታ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም ዳኛው ሰአት ሄዷል በሚል ለሰኔ 17 ቀን 2006 ዓም ቀጠሮ ሰጥተዋል።
ለምስክርነት የቀረቡት ፖሊሶች ኢንስፔክተር በለጠ በቀለ፣ ኢንስፔክተር ምትኩ ደሳለኝ፣ ኮማንደር አሰፋ ወልዴ፣ ፖሊስ ኦላና ተስፋ፣ ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ ኪዳኔ ሲሆኑ፣ የቡራዩ የወጣቶች ቢሮ ሃላፊ የሆነው መስፍን ለማም በተከሳሾች ላይ ለመመስከር ቀርቧል።
አቃቢ ህግ ፖሊሶችን እና የኢህአዴግ ባለስልጣንን በምስክርነት ለማቅረብ የተገደደው ብዙዎቹ የአካባቢው ሰዎች በተከሳሾች ላይ ለመመስከር ፈቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው ነው። አቃቢ ህግ በገንዘብ ምስክሮችን የመግዛት እንቅስቃሴ ቢጀምርም እስካሁን እንዳልተሳካለት የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌሎች 3 ወጣቶች ምንም አይነት ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።