የባህር ዳር ባጃጅ አሽከርካሪዎች አድማ መተው አረፈዱ

ሰኔ ፬(አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰኔ 4 ቀን 2006 ዓም ከንጋት ጀምረው አድማ መተው ያረፈዱት የባህር ዳር ከተማ ባጃጅ አሺከርካሪዎች ፤ መንግስት ለጥያቂያችን ምላሺ እስካልሰጠ ድርስ የስራ ማቆም አድማው ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ከሶስት ሺህ በላይ ባጃጆች የሚርመሰመሱባት ባህርዳር ከጎዳናዋ የተሰወሩባት ከንጋቱ  ጀምሮ ከከተማዋ ተሰውረው ህብረተሰቡ እና መንግስት ሰራተኛው በትራንስፖርት ችግር ውስጥ ወድቆ አርፍዷል፡፡

የባጃጅ አሺከርካሪ ማህበራትሃላፊነቱን በወሰዱበት በዚህ አድማ ፣ “የመንግስት  ባለስልጣናትን ወደ ከተማዋ መግባት ተከትሎ  ነዳጅ እንከለከላለን፣  ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ አታደምቁም ተብለን እንዳንሰራ ታግደናል፣  የምሺት ባጃጆች በቀን እንዳይሰሩ እገዳ ተጥሏል ይነሳልን” የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

“መንግስት ነዳጅን ለማደል  የድጋፍ ሰልፍ መውጣትን እንደመመሪያ ማድረጉ፣ ባለስልጣን በመጣ ቁጥር  ፍተሻው ማስመረሩ፣  ባለስልጣን በመጣ ቁጥር ከምንሰራበት ቁመን የምንውልበት ቀን መብለጡ፣ ቀን የሚሰሩ ባጃጆች በምሺት እንዳይሰሩ መከልከሉ መንግሰትን ለመቃወም ምክንያት ሆኖናል” ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ አስተያየት ሰጪዎች ለዘጋቢያችን ገልጸውላታል።

የክልሉ ንግድ እና መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ  “ባሰቸኳይ  ስራ ያልጀመረ መንጃ ፍቃድ ይነጠቃል” የሚል  ማስታወቂያ ቢያወጣም አድማው እስከ አምስት ስዓት ቀጥሎ ውሎአል። መንግስት ከባጃጅ ማህበሮች ጋር ባደረገው ውይይት ችግሩን እንደሚያቃልል ቃልበመግባቱ እና የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ በመደረሱ ባለባጃጅ መኪኖቹ ወደ ስራ ተመልሰዋል።