ፕሬዚዳንት ኦባማ በአፍሪካ ጉብኝታቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እንዲደግፉ ተጠየቁ

ሰኔ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ዛሬ በሚጀምሩት የሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካና ታንዛኒያ ጉብኝት በችግር ተዘፍቀው የሚገኙትን የአፍሪካ የመገናኛ ብዙሀንንና የሰአብአዊ መብቶች ተሟጋቾችን እንዲደግፉ ሂውማን ራይትስ ወች ጠይቋል።

በአፍሪካ መገናኛ ብዙሀንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች ከፍተኛ የሆነ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ፕሬዚዳንቱ ጉብኝት የሚያደርጉባቸው ደቡብ አፍሪካ፣  ሴኔጋልና ታንዛኒያ ሀሳብን በነጻነት በመግለጽ እና በፕሬስ ነጻነት ዙሪያ የተሻለ ሁኔታ ቢኖርም በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ በመሆኑ ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ትኩረት እንዲሰጡ ድርጅቱ ጠይቋል።

የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት  ዳንኤል በቀለ ፕሬዚዳንት ኦባማ የአፍሪካ ጋዜጠኞች እና የሲቪክ ማህበረሰቡ አባላት ለሚያሳዩት ጥንካሬ እውቅና መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ በርካታ ጋዜጠኞች አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን የገለጸው ድርጅቱ፣ ኢትዮጵያ የጸረ ሽብር ህግን በመጠቀም  11 ጋዜጠኞችን መክሰሷን አመለክቷል።

የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት አፍሪካ የሰራቻቸውን ስራዎች ማጉላት ብቻ ሳይሆን፣ የሰብአዊ መብቶችን ማክበር ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገር አለባቸው በማለት አቶ ዳንኤል ገልጸዋል።

 ፕሬዚዳንት ኦባማ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት ሲጎበኙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ነው። በማደግ ላይ ያለችው ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ያላት ቦታ እየተጠናከረ መምጣት ለፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ምክንያት መሆኑን አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ።

 ፕሬዚዳንቱ የሚጎበኙዋቸው ሶስቱ አገራት በአፍሪካ የተሻለ ዲሞክራሲን መገንባታቸው ይነገርላቸዋል።