የደኅንነት ሠራተኞች ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ለሚወስዱት ዕርምጃ በሕግ አይጠየቁም ተባለ

ሰኔ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተቋምን በሚኒስቴር ደረጃ እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ የደኅንነት ሠራተኞች ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ለሚወስዱት ዕርምጃ በሕግ እንደማይቀጡ ተመለክቷል።

ሪፖርተር እንደዘገባው ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት በ1987 ዓ.ም. በወጣ አዋጅ የተቋቋመ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በርካታ አገራዊ፣ አካባቢያዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ላይ ለውጦች መታየታቸውና እነዚህ ለውጦች በኢትዮጵያ ደኅንነት ላይ ያላቸውን ፋይዳ ባገናዘበ ሁኔታ በተቋሙ ላይ ለውጥ መፍጠር በማስፈለጉ፣ ማሻሻያው እንዲደረግ ተወስኗል።

አገልግሎቱ ካለበት ሕገ መንግሥታዊና አገራዊ ኃላፊነት እንዲሁም ካለው ሰፊ ሥልጣንና ተግባር አንፃር በሚኒስቴር ደረጃ እንዲዋቀር መፈለጉ በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡

ተቋሙ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን የሒሳብ መዛግብትና ሌሎች የሥራ መረጃዎችን እጅግ ብርቱ ምስጢር ብሎ በመሰየም  የፈዴራል ኦዲተርን ጨምሮ ለሌሎች አካላት ሊከለክል ይችላል።

ይህ ሥልጣን ቢኖረውም በውስጥ ኦዲተርና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀርብ ሪፖርት መነሻነት ክትትልና ቁጥጥር ስለሚደረግበት፣ የተጠያቂነት ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ የማያጭር መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አባሪ መግለጫ ማመልክቱ ተዘግቧል።

ተቋሙ ከውጭ አገር የሚያስገባቸውን የመረጃ ደኅንነት መሣሪያዎች ወይም ዕቃዎች ለጉምሩክ ሳይገለጹ እንዲገቡ ማድረግ ሲችል፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ተመሳሳይ መሣሪያዎች ሚስጥራዊ ባህሪያቸው እንደተጠበቀ እንዲንቀሳቀሱ አዋጁ ይፈቅዳል፡፡

የተቋሙ የደኅንነት ሠራተኞች ማንነትና የሀብት መጠን ሚስጥራዊ በሆነ ሁኔታ እንዲጠበቅ የማድረግ ኃላፊነትም በረቂቁ ተካቷል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙ ከአገር ውስጥ የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በፀጥታ ዙሪያ በቅንጅት እንዲሠራ ትብብሩና መደጋገፉ በአጋር አካላት በጐ ፈቃደኝነት ላይ የተሠረተ ሳይሆን፣ ግዴታን የጣለ ረቂቅ አንቀጽ ተካቷል፡፡

የአቪዬሽን ደኅንነትን በበላይነት የመምራት፣ ብሔራዊ የመታወቂያ ካርድ የመስጠት ሥራን በበላይነት የመምራት፣ እንዲሁም ለግል ጥበቃ ድርጅቶችና ሠራተኞች የማረጋገጫ ሠርተፊኬት የመስጠት ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል፡፡

የተቋሙ የደኅንነት ሠራተኛ ኃላፊነቱን በአግባቡ በሚወጣበት ወቅት በነበሩ አስገዳጅ ሁኔታዎች ለሚወስደው ዕርምጃ በወንጀልም ሆነ በፍትሐ ብሔር ወንጀል እንደማይጠየቅ ረቂቁ ያስረዳል፡፡

የደኅንነት ሠራተኞች በሥራ ላይም ሆነ ከተሰናበቱ በኋላ በሥራ አጋጣሚ የሚያውቋቸውን ሚስጥሮች የመጠበቅ ግዴታ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው በተቋሙ መረጃ ተጠይቆና ሰጥቶ ስለመሆኑ በቸልተኝነት እንኳን ለሌሎች ቢያሳውቅ በወንጀል እንደሚጠየቅ ረቂቅ አዋጁ ይገልጻል፡፡

በተጨማሪም የተቋሙ ሠራተኛ ያልሆነ ግለሰብ በተቋሙ፣ በኃላፊው ወይም በደኅንነት ሠራተኞች ስም በቃል ወይም በድርጊት ለማታለልና ለማስመሰል የሞከረና የተቋሙን ተግባር ያወከ ግለሰብ፣ በወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች እንደሚቀጣ በረቂቁ ተካቷል፡፡ ረቂቁ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት ተመርቷል፡፡