ሰኔ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የሚኖሩ ነዋሪዎች ፓዌ በፊት ትጠራበት ወደነበረው ልዩ
ወረዳነት እንድትመለስ በመጠየቃቸው ከፍተኛ እንግልት እና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን ፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በወረዳዋ የሚኖሩ ወጣቶች በጋራ እንደገለፁልን ከ1977 ዓ.ም በፊት ከሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በሠፈራ መጥተው ፓዌ ወረዳ ላይ የቆዩ ሲሆን በ1983 ዓ.ም በአካባቢው ከሚኖሩ ጉምዝ፣ ሺናሻ፣ ርታ፣ ማኦ እና ኮሞ ተወላጆች ጋር እርስ በርስ የተፈጠረውን ግጭት ለማስማማት በወቅቱ በነበሩት ጠ/ሚ ታምራት ላይኔ ውሣኔ መሠረት ፓዌ ልዩ ወረዳ እንድትሆን መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በቅርቡ በክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ አህመድ ናስር አማካኝነት ፓዌ ልዩ ወረዳ መባሉዋ ቀርቶ ፓዌ ወረዳ ብቻ እንድትባል በመወሰኑና ውሳኔውን ባለመቀበላችን የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተገኙበት ተሰብስበን ጥያቄ ብናቀርብም ፣ አቶ ገዱም መኢአድ ፓርቲን ምረጡ እንጂ እንደ እናንተ አይነት አማራ አናውቅም በማለት ልዩ ወረዳ መሆኑን ሣይቀበሉት መቅረታቸውን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፡፡
አማራ ክልልን ከቤኒሻንጉል በሚያዋስነው ኬላ ላይ ፓዌ ልዩ ወረዳ የሚል መታወቂያ ይዘው የተገኙ ተወላጆች ላይ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊሶች ከፍተኛ ድብደባ በማድረስ ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን መታወቂያ ካርድ ተቀበለው የሰበሰቡ ሲሆን ልዩ ወረዳ የሚል መታወቂያ ይዞ በክልሉ ሆቴል ቤቶች አልጋ መያዝ እንዳልተቻለም ጠቁመዋል፡፡
ፓዌ ልዩ ወረዳ በነበረችበት ወቅት ከሁሉም ብሄር የተወጣጡ አስተዳዳሪዎች ሲያስተዳድሩዋት እንደነበር የጠቀሱት ነዋሪዎች በአዲሱ ውሳኔ መሰረት የወረዳው ሕግ አስፈፃሚ የአንድ ብሄር ተወላጆች ብቻ እንዲሆን መደረጉ እየደረሰብን ያለውን ጫና አባብሶብናል ብለዋል። የፌዴሬሽን ም/ቤት አስቸኳይ መፍትሄ ይሰጠን ሲሉም ጠይቀዋል። ፔዌ በደርግ ዘመን የተጀመረውን የጣና በለስ ፕሮጀክት ምክንያት በማድርግ ከተለያዩ አካካቢዎች ተሰባስበው የሄዱ ኢትዮጵያውያን የመሰረቱዋት ከተማ መሆኑዋ ይታወቃል።