በማዳበሪያ እዳ ለስደትና ለእንግልት ተዳርገናል ሲሉ አርሶ አደሮች ተናገሩ

ሰኔ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሺንዲ ወንበርማ ወረዳ የማንችለውን ውዝፍ የማዳበሪያ እዳ እንድንከፍል በመገደዳችን ለስደትና እንግልት ተዳርገናል ሲሉ በርበሬ አምራች አርሶ አደሮች ተናግረዋል ፡፡

በመንግስት በታጠቁ ሀይሎች ሀብት ንብረታችን ተዘርፎና የቤታችን ቆርቆሮው ተገፎ ተወስዶብናል ያሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አርሶ አደሮች፣  ዛሬ ቤት ንብረታችንን ጥለን ቤተሠባችንን በትነን ለስደት ተዳርገናል ብለዋል።
በአየር ንብረት መዛባት ችግር በደረሰብን አደጋ ምርታችን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ በመቻሉ ምክንያት ወዝፍ የማዳበሪያ እዳ መክፈል አልችል በማለታችን እንግልቱ ደርሶብናል ሲሉ አማረዋል፡፡

መንግስት ሊደግፈን ሲገባ   ማሳደዱና መንገላታቱ ከፉኛ አሳዝኖናል ያሉት አርሶአደሮቹ ችግራቸው ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ መንግስት እንዲያሻሽልላቸውም ተማፅነዋል፡፡

የበርበሬ ምርት በቀላሉ ለብልሽት የሚዳረግ በመሆኑ በደረሰው የአየር ንብረት መዛባት ምርታችን በሜዳ ስለቀረ እዳችንን መከፈል ተስኖናል ያሉት አርሶ አደሮች ይህ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ መንግስት ህዝቡ ላይ ባሳደረው የእዳ ጫና ማዳበሪያም ሆነ ምርጥ ዘር የሚያወጣው አርሶ አደር ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል ብለዋል፡፡

ሺንዲ ወንበርማ ወረዳ  በበርበሬ አምራችነቷ ብቻ ሳይሆን በምርጥ ዘር ብዜት ማዕከልነቷ ወሳኝ የሚባል ሀገራዊ ሚና አላት።  ተፈጥሮ ባመጣው ክስተት እዳቸውን መክፈል ያልቻሉ አርሶ አደሮች በመንግስት ለእስርና ለስደት መዳረጋቸው፣  የስንዴም ሆነ የበቆሎ ምርጥ ዘር ለማባዛት  ወደ ኋላ እንዲሉ እንዳደረጋቸው  አርሶ አደሮቹ ይናገራሉ።

ከማዳበሪያ እዳ ጋር በተያያዘ በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎችም ከፍተኛ የሆነ ሮሮ እየተሰማ ነው። መንግስት በግዴታ የሚያከፋፍለውን ማዳበሪያ በመውሰድ እዳ ውስጥ የገቡ የደቡብ ክልል አርሶ አደሮች ቤት ንብረታቸውን እየሸጡ እስከ መሰደድ ደርሰዋል።

የኢትዮጵያን ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡት የገዢው ፓርቲ ኩባንያዎች መሆናቸው ይታወቃል። የኢህአዴግ ካድሬዎች  በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ገበሬው ያለበትን የማዳበሪያ እዳ በማስከፈል ነው። በማዳበሪያ  እዳ ምክንያት  ቤት ንብረታቸው አፍረሰው የተሰደዱ አርሶ አደሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በግብርና ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት መናገራቸው ይታወቃል። መንግስት የገዢውን ፓርቲ ኩባንያዎች ጥቅም ከማስጠበቅ ውጭ ችግሩን ለመቅረፍ እስካሁን መሰረታዊ ሆነ እርምጃ ሲወስድ አልታየም።