ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣን ማተሚያ ቢቶች ሁሉ አናትምም አሉ

ህዳር ፲፯ (አስራ አምት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የአንድነት ለዲሞክራሲና የፍትህ ፓርቲ ልሳን የሆነችው ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ በየትኛውም ማተሚያ ቤት እንዳይታተም መደረጉ ተገለጸ ፤ ጋዜጣዋን ሲያትሙ የነበሩ የግል ማተሚያ ቤት ባለቤቶች ላይ ማስፈራራትና ዛቻም ተፈጽሞል።

የአንድነት ፓርቲ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዳነኤል ተፈራ ከኢሳት ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት የፍኖተ ነጻናት ጋዜጣ ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቀርበው 34 ማተሚያ ቤት አለ በነሱ ማሳተም ይችላሉ ቢሉም ካድሬዎቻቸውና ደህንነታቸው በየማተሚያ ቤቱ በመዞር ማስፈራራትና ዛቻ በመፈጸም ጋዜጣዋ በየትኛውም ማተሚያ ቤት እንዳትታተም አድርገዋል ብለዋል።

ይህንን የረቀቀ አፈና ለመታገልና ለመስበር ፓርቲያቸው የተለያዩ ዘዴዎችን ለመቀየስ ተገዶል ያሉት አቶ ዳነኤል ለጠቅላይ ሚኒስትር ፣ ለብሮድ ካስት ኤጀንሲና ለኮምንኬሽን ጽ/ቤት ደብዳቤም ቢጽፉም መልስ የሚሰጣቸው እንዳላገኙ ተናግረዋል።

የግል ማተሚያ ቤቶችን አዳርሰናል መጀመሪያ እሺ ብለው ከተስማሙ በሆላ ፍኖተ ነጻነት መሆኖን ሲያውቁ አሻፈረን ይላሉ ያሉት የህዝብ ግንኙነቱ በተለይ አንዱ ማተሚያ ቤት የመጀመሪያ ዙር አትሞ ካወጣ በሆላ ሁለተኛው እትም ሳያልቅ አላትምም ማለቱን ተናግረዋል።

እነዚህ የማተሚያ ቤት ባለቤቶችም በመንግስት ሰዎች ማስፈራሪያና ዛቻ እንደደረሰባቸው በስጋት እንደነገሮቸው አጋልጠዋል አቶ ዳነኤል።

ስለዚህም ጋዜጣችው ከሀገሪቱ የህትመት ስራት ውስጥ እንድትወጣ ተደርጎል፤ ግን ደግሞ ማተሚያ መሳሪያ በመግዛት ጭምር እስከ መጨረሻው ይህንን የረቀቀ የአፈና ድርጊት እንደሚታገሉት አስታውቀዋል።