ሐምሌ ፲፭ (አስራአምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ድረስ ለተጠቀሱት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ሆነው አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲቀርቡ ሲል የልደታ ፍርድ ቤት 19 ኛው የወንጀል ችሎት ወሰነ፡፡የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በምስክርነት እንዲያቀርብ ሲል ፍርድ ቤቱ ለሀምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥትዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሀምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ልደታ ፍርድ ቤት ቀርበው የመከላከያ ምስክር እንዲሆኑ ፍርድ ቤቱ ወስኖ የነበር ቢሆንም፣ ይገኙበታል ለሚባሉት ማረሚያ ቤቶች በተለይም ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚላከው ማዘዣ ዘግይቶ በመላኩ እንዳልደረሰለት ገልጾ ለዛሬ ሀምሌ 15 ቀን 2007 ለምስክርነት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ሆኖም አቶ አንዳርጋቸው ዛሬም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ለምን እንዳላቀረበ የተጠየቀው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ማዘዣው እንደደረሰው ገልጾ ነገር ግን ማዘዣው ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተብሎ መፃፍ ሲገባው ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተብሎ በመፃፉ አቶ አንዳርጋቸውን ማቅረብ እንዳልቻለ ገልጾአል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ማዘዣው ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተብሎ ተፅፎ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሀምሌ 29 ቀን 2007 ለመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት 10 ግለሰቦች መካከል ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝታችኋል የሚል ክስ የቀረበባቸውና አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት እንዲመሰክሩላቸው የጠሩት አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛ፣ አቶ ማንዴላ ጥላሁን፣ አቶ አንሙት የኔዋስና አቶ አሰፋ ደሳለኝ መሆናቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።