በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪ ደላሎች ታግተው ገንዘብ እንደሚጠየቁ ዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም አስታወቀ

ሐምሌ ፲፭ (አስራአምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም በየመን አድርገው በሕገወጥ መንገድ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመግባት ሲሞክሩ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ታግተው የአካልና የሞራል ጉዳት የደረሰባቸውን ቁጥራቸው 3 ሺ 478 የሚሆኑ በጎፈቃደኛ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው መመለሱን አስታውቀዋል።
የ18 ዓመቱ ወጣት አልማይ ፍፁም ”በመኪና ተጭነን ወደ ሳዑዲ ድንበር እንደተቃረብን ፤ መሳሪያ ያነገቡ ታጣቂዎች ወደ እኛ መተኮስ ጀመሩ አብዛኞቻችን ተመተናል፤ሁለቱ ጓደኞቻችን ወዲያውኑ ሞተዋል! መኪናው ቆመና በታጣቂዎች ተያዝን” ሲል ስለደረሰባቸው ጉዳት ተናግሯል።
የጥቃት ሰለባ የሆነው የ20 ዓመቱ ወጣት ተመላሽ ስደተኛ ቃሲም የሱፍ በበኩሉ ”ከሰሜን ወሎ ዞን ነው የመጣሁት፣ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ታገትኩኝ እየደበደቡኝ ስልክ ይሰጡኝና እቤት ደውዬ ገንዘብ እንዳስልክ ያደርጉኛል። ቤተሰቦቼ ያላቸውን 5 ሺ ሪያል በምንዛሬ 1 ሺ 333 ዶላር ቤተሰቦቼ የእኔን ሕይወት ለማትረፍ ከጎረቤት እየተበደሩ ልከውልኛል።ገንዘብ ካልላኩ በተቃጠለ ፕላስቲክ አካላቴን በማቃጠል ያሰቃዩኛል! የታገትኩበትን ገንዘብ ከፍዬ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ድንበር ስንቃረብ እኛን በጫነችው መኪና ላይ የአውሮፕላን ድብደባ ጥቃት ተፈፀመብን።” በማለት የደረሰበትን ሰቆቃ ተናግርዋል።
ሌላው ተመላሽ የ20 ዓመቱ ወጣት መላኩ ጥዑማይ ”የመጣሁት ከአላማጣ ትግራይ ሲሆን ምንም ዓይነት አካላዊ ጉዳት ሳይደርስብኝ በሰላም በመመለሴ ግን ዕድለኛ ነኝ!” ብሏል።
”የፍየል እረኛ፣የፋብሪካ ሰራተኛ፣የጥበቃ ስራዎች በሳዑዲ አረቢያ እንዳለና ጥሩ ክፍያም እንደሚከፍሉ ሰማሁ፤ አባቴ ሞትዋል ቤተሰባችንን የማስተዳድረው እኔ ነኝ። ለደላሎች የጀልባ የከፈልኩት እራሴው ነኝ። 53 ሆነን ለስድስት ሰዓታት ተጉዘን የመን ገባን።እዛ እንደደረስን ግን ዕድለኞች አልነበርንም አጋቾች እጅ ላይ ወደቅን!” ሲል ተናግሯል። ”እኔና ሦስቱ ጓደኞቼን አጋቾቹ ይዘው ወደ ስውር ቦታ ወሰዱን። እየደበደቡ ገንዘብ እንድናስልክ አስገደዱን፣ ሳዑዲ ያለችው እህቴ 4 ሺ 500 ሪያል በምንዛሪ1 ሺ 199 ዶላር ከፍላ እንድለቀቅ አደረገችኝ።” ሲል አክሏል።
ባለፉት ሶስት ሳምንታት ከተመለሱት ስደተኞች ውስጥ 57 የሚሆኑት በመሳሪያ የቆሰሉ፣ የተቃጠሉ፣ አጥንታቸው የተሰበሩ ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን በሙሉ አውጥተን ጨርሰናል” ማለታቸው አይዘነጋም። ሆኖም ግን አሁንም በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎቻችን ከፍተኛ እንግልትና ሰቆቃ እየደረሰባቸው መሆኑን ዓለማቀፍ የስደተኞች መብት ተከራካሪዎች እየገለፁነው።በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM የገንዘብ ዕርዳታ መለገሳቸው ያታወሳል።