የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነፃና ገለልተኛ ሆኖ፣ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ ውጤታማ ሥራ ሠርቷል ማለት እንደማይቻል የቀድሞ ኮሚሽነር አስታወቁ

ሐምሌ ፲፭ (አስራአምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት አቶ ጌታሁን ካሳ ”የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋም ሚናውና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ ይጋጠሙት ፈተናዎች” በተሰኘ ጥናታዊ የምርምር ሥራቸው ላይ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተቋም ነፃና ገለልተኛ ሆኖ፣ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ ውጤታማ ሥራ ሠርቷል ማለት እንደማይቻል አመልክተዋል፡፡አቶ ጌታሁን ኮሚሽኑ ሰብዓዊ መብትን ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ጥቆማዎች ላይ ምርመራ በማድረግ፣ ወቅቱን የጠበቀና ተከታታይነት ያለው የሰብዓዊ መብት ይዞታ ሪፖርት በማቅረብና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የመከላከል ሥራው ላይ ደካማ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ሌላው ጥናት አቅራቢ አቶ መሐመድ በበኩላቸው ”ኮሚሽኑ ፖለቲካዊ ትኩሳት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ራሱን እንደሚያገል የጉራፈርዳን ተፈናቃዮች ጉዳይ በምሳሌነት በማንሳት ተናግረዋል። “የሚወጡ ሕጎች የሰብዓዊ መብት መሥፈርቶችን ስለማክበራቸው አስተያየት አለመስጠቱ፣መንግሥታዊ ካልሆኑ በሰብዓዊ መብት ላይ ከሚሠሩ ተቋማት ጋር ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት መፍጠሩ፣የመንግሥትን የሰብዓዊ መብት ሪከርድ በአደባባይ መከላከሉና ለአብነት ከሂዩማን ራይትስ ዎች ጋር የተመላለሰው ደብዳቤ ግልጽነት የሌላቸው አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ሥጋት የፈጠሩና ተቋሙን ወደኋላ የጎተቱ ችግሮች መሆናቸውን አቶ መሐመድ አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተቋሙ በሕዝቡና በሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ዓይን ነፃና ገለልተኛ ሆኖ እንዳይታይ እንዳደረጉትም አመልክተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ሌላ የሚተችበት ጉዳይ ፓርላማው የሚያወጣቸው ሕጎች ከሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን አረጋግጦ አለማወቁ ነው፡፡ አምባሳደር ጥሩነህ በሕጎቹ ላይ አቋም አለመውሰድ ክፍተት መሆኑን ቢያምኑም፣ ፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የሚባለውን ያህል ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ ሳይሆን ኢትዮጵያ የተሻለች እንድትሆን አስተዋጽኦ አድርጓል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ላይ ግን ጥናት እየተደረገበት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
አቶ ታምሩ አምቤሎ የሚኖሩበት የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአካባቢያቸው የሚገኘውን ጫካ ለሻይ ቅጠል አምራች ኩባንያ መስጠቱ የመብት ጥሰት ነው በማለት፣ ቅሬታቸውን በአካባቢው ነዋሪ ኅብረተሰብ ስም ‹‹ከመኖሪያ ቤታችንና ከእርሻችን በኃይል መፈናቀላችን፣ የመሥራትና ኑሮን የመደገፍ እንዲሁም ራሳችን ከአካባቢያዊ ተፅዕኖ የመጠበቅ መብታችን ተጥሷል›› በማለት አቤቱታቸው ለኮሚሽኑ በግንቦት ወር 2003 ዓ.ም. ቢያቀርቡም ኮሚሽኑ በወቅቱ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የለኝም በማለት ለመመርመር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
አቶ መሐመድ ‹‹ነፃ፣ ብቃት ያለውና ቆራጥ መሪ›› ኮሚሽኑን በአዲስ አቅጣጫ ለመውሰድና ለሰብዓዊ መብት የሚቆም ተቋም ሊያደርገው እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን ግን የዕጩዎች መረጣና ጥቆማ የሕዝብ ተሳትፎና አስተያያትን እንዲያካትት አዋጁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል ማለታቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።