(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 29/2010) በኢትዮጵያ የኢሕአዴግ መርህ እየተተወና ፈላጭ ቆራጭ አመራር እያደገ መጥቷል ሲሉ የሕወሃት አመራሮች ገለጹ።
የሕወሃት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልና የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለም ገብረዋህድ ከክልሉ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል።
በዚሁ ውይይትም ኢትዮጵያ ባለፉት 17 አመታት ካስመዘገበችው እድገት ውጪ አዲስ ለውጥ የለም ሲሉ ገልጸዋል።
እኛ የቀን ጅቦች አይደለንም በኢሕአዴግ ውስጥ ግን በአራቱም አባል ድርጅቶች ውስጥ የቀን ጅቦች አሉ ብለዋል።
የሕወሃቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልና የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚና የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አለሙ ገብረዋህድ በኢትዮጵያ የሕገ መንግስት መሸርሸር እያጋጠመ ነው ብለዋል።
በተለይ አቶ አለም ገብረዋህድ ለተሰብሳቢዎቹ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንደተናገሩት “ኢሕአዴግ መንታ መንገድ ላይ ይገኛል።እናም ኢሕአዴግ አበቃለት ብለን ከምንተወው እስከመጨረሻው እንታገላለን” ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ባለፉት 17 አመታት ከመጣው ለውጥ ውጭ አዲስ ለውጥ የሚባል ነገር የለምም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአፋር ባካሄዱት ስብሰባ የኢትዮጵያ ጦር ከኤርትራ ድንበር ወሰን ይነሳል ስለማለታቸው ያላቸውን ስጋትም ተሰብሳቢዎቹ ጠይቀው ነበር።
አቶ አለም ገብረዋህድ ግን የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት ዘላቂ የሰላም መፍትሄ ካልመጣ በስተቀር ጦሩ ከአካባቢው በፍጹም አይንቀሳቀስም ብለዋል።
“የኛን ሰላም ለአደጋ አጋልጠን ለሌላው ሰላም ዋጋ አንከፍልምም”ብለዋል።
የሕወሃቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ከሕወሃት በተለያዩ ምክንያቶች የለቀቁ የቀድሞ አመራሮች ለምን ተመልሰው በዚህ የችግር ወቅት አይረዱንም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
የቀድሞ አመራሮችን ግማሽ መንገድ ድረስ ሄድን እንቀበላቸዋለን፣ያ ማለት ግን እነሱ ብቻ ናቸው መፍትሄ ማለት አይደለም ብለዋል።
ዶክተር አረጋዊ በርሄ የቀድሞ መሪዎችን በሌላ አቋም ቢቆይ እንኳ ወደኛ ከመጣ እንቀበለዋለን ነው ያሉት።
የቀን ጅቦች ለምን እንባላለን በሚል ከመድረኩ ለቀረበላቸው ጥያቄም “የቀን ጅብ ከሕወሃት ብቻ ሳይሆን ከአራቱም የኢሕአዴግ ድርጅቶች አለ” ብለዋል።