በሶማሌ ክልል እስረኞችን ማሸሽ ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 29/2010)የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ እስረኞችን በማሸሽ ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ከፍተኛ ሰቆቃ የሚፈጸምበት ጄይል ኦጋዴን ዛሬ ከ20 አዳዲስ እስረኞች በቀር በሺዎች የሚቆጠሩ ግፍና ስቃይ የደረሰባቸው እስረኞች በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች ወደሚገኙ እስርቤቶች እንዲሸሹ መደረጋቸውን የኢሳት የመረጃ ምንጮች አጋልጠዋል።

ጄል ኦጋዴንን ጨምሮ በሶማሌ ክልል ለተፈጸሙ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሆነው አብዲ ዒሌ በአሰቃቂው እስር ቤት ማስረጃዎችን በማጥፋት ላይ መሆኑም ተገልጿል።

ትላንት የዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች ጠንከር ያለ ሪፖርት ያነጣጠረው በሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳን አብዲ ዒሌ ላይ ነው።

ግለሰቡ በጄል ኦጋዴን እየፈጸመ ያላቸው ወንጀሎች በዝርዝር ከቀረበ በኋላ በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ምክረ ሀሳብ የሚሰጥ ሪፖርት ነው።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት አብዲ ኢሌ በሺዎች የሚቆጥሩ በጄል ኦጋዴን የሚገኙ እስረኞችን አሽሽቷል።

ሪፖርቱ እንደሚወጣ መረጃው ከደረሰው ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ እስረኞችን በማጓጓዝ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች እንዳስቀመጣቸው የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

ባልፉት ቀናት ከጄል ኦጋዴን የተወሰዱት እስረኞች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሰቆቃ የተፈጸመባቸው መሆኑም ታውቋል።

ከትላንት ጀምሮ ጄል ኦጋዴን ባዶ እንዲሆን መደረጉን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች የእስር ቤቱን ክፍሎች በአዲስ መልክ የመገንባት ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።

ሪፖርቱ መውጣቱን ተከትሎም በአብዲ ዒሌ ዙሪያ ከፍተኛ መረበሽ መፈጠሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የክልሉ መንግስትን እንቅስቃሴ በተመለከተ መረጃ የሚያቀርበው ካካራ ኒውስ የተባለ ድረ ገጽም የአብዲ ዒሌን ምላሽ  ይዞ ወጥቷል።

ጄል ኦጋዴን ከ20 በላይ እስረኞች እንደሌሉ የገለጸው የአብዲ ዒሌ አስተዳደር እስር ቤቱ በዘመናዊ መልክ የተገነባ በያንዳንዱ ክፍል ቴሌቪዥን በመትከል እስረኞች መረጃ እንዲያገኙ የሚደረግ ነው ብሏል።

እስር ቤቱ የመዝናኛ ስፍራ ያለው እስረኞች አእምሮአቸውን አሳርፈው የሚቆዩበት ማዕከል ነው በማለት አብዲ ዒሌ ምላሽ ሰጥቷል።

በሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት የተደናገጠው አብዲ ዒሌ መረጃና ማስረጃዎችን በማጥፋት ላይ መሆኑም ታውቋል።

ለዓመታት ሰቆቃ ሲፈጸምበት የነበረውን ጄል ኦጋዴንን ባለፉት ሶስት ቀናት የወንጀል ዱካ እንዲሰወር በማድረግ ላይ መሆኑንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

አብዲ ዒሌ ከእስረኞቹ በተጨማሪ በእስር ቤቱ ጠባቂዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባና ሰቆቃ እንዲፈጸም የሚያስደርግ ሲሆን ይህንምም መረጃ ለመሰወር እንደሆነም ምንጮች ገልጸዋል።

ሂውማን ራይትስ ዎች በትላንቱ ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሶማሌ ክልል እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲመረምሩ ጥሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።