(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 4/2010) ጣሊያን በባህር ድንበሯ ተሻግረው ሊገቡ የነበሩ ስደተኞችን አገደች።
አዲሱ የጣሊያን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እገዳውን ያስተላለፉት በነፍስ አድን ሰራተኞች ከባሕር ላይ ሕይወታቸው ተርፎ ወደ ጣሊያን ሊገቡ የነበሩ 629 ስደተኞችን ነው።
ከሊቢያ አቅራቢያ ከተለያዩ ጀልባዎች በነብስ አድን ሰራተኞች ድጋፍ ከአደጋ የተረፉትን 629 ስደተኞች ነው የጣሊያን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደማይቀበል ያስታወቀው።
ስደተኞቹ ከ6 የተለያዩ ጀልባዎች በጀርመን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ርብርብ የተረፉ መሆናቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።
ነገር ግን ጣሊያን በሩዋን በመዝጋቷ ሳቢያ ሜዲትራኒያን ባህር ላይ በጀልባቸው ውስጥ ሆነው መጪውን ጊዜ መጠባበቅ ግድ ብሏቸዋል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤትና የአውሮፓ ህብረት በጋራ በጣሊያንና ሊቢያ መካከል እየደረሰ ስላለው የሰብአዊ ቀውስ አፋጣኝ መፍትሄ ለመፈለግ ጥሪ ማድረጋቸው ታውቋል።
በቅርቡ የተሾሙት የጣሊያኑ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማቲዮ ሳልቫኒ ህገወጥ የሰው ዝውውርን እንደሚያወግዙና በዚያ መንገድ የሚመጡ ስደተኞችን እንደማይቀበሉ በተመረጡበት ወቅት መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ይህንንም ቃላቸውን ዛሬ ላይ ከአደጋ ተርፈው ወደ ጣሊያን የባህር በር በደረሱ 629 ስደተኞች ላይ ተግባራዊ አድርገውታል።
በጀልባዋ ውስጥ ደግሞ 123 ህፃናት መኖራቸውን መረጃዎቹ አመልክተዋል።
ለሰአታት በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ከጀልባቸው መውረድ ባለመቻላቸውም መዳከማቸውን ነው ቢቢሲ በዘገባው ያመለከተው።
በነፍስ አድን መርከቧ ውስጥም ከኤርትራ፣ ሱዳንና ናይጀሪያ የመጡ ስደተኞች እንደሚገኙም ታውቋል።
ይህ ዜና እየተጠናቀረ ባለበት በአሁኑ ሰአትም ስፔን ስደተኞቹን እንደምትቀበል መግለጿ ተሰምቷል።
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ፔርዶ ሳንቼዝ ሊደርስ የሚችለውን የሰብአዊ ቀውስ ለመታደግ በማሰብ ሴፍ ሀርበር ለተባለችው የስደተኞች መርከብ በራቸውን እንደሚከፍቱ አስታውቀዋል።